የአዲስ አበባ ከተማን ልማት ለማፋጠን የምናበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክረን እንቀጥላለን - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማን ልማት ለማፋጠን የምናበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክረን እንቀጥላለን
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦የአዲስ አበባ ከተማን ልማት ለማፋጠንና ሰላም ለማጽናት የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሃይማኖት አባቶች እና አባ ገዳዎች ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ከሃይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከአባ ገዳዎች፣ ከሀደ ሲንቄዎችና ጥሪ ከተደረገላቸው እንግዶች ጋር ከተማ-አቀፍ ኮንፈረንስ አካሂዷል።
በዚሁ ወቅት የየካ ክፍለ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ዋና ሰብሳቢ መልዓከ-ኃይል አባ ኃይለገብርኤል ከተማ፤ የሃይማኖት ተቋማት ለምዕመናን ሃይማኖታዊ ትምህርትን ከመስጠት ባሻገር ግብረ ገብን የተላበሱ እንዲሆኑ የማስተማር ተልዕኮ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
በግብረ ገብ ታንጾ ያደገ ትውልድ ልማትን ለማፋጠንና ለዘላቂ ሰላም ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ቤተ እምነቶች የመዲናዋን ሰላም ለማጽናት የምናበረክተውን አስተዋጽኦ አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት ሼህ መሐመድ ሸሪፍ በበኩላቸው፤ የከተማዋን ሰላም ማስጠበቅ የተቻለው መንግስት እና ህዝብ በጋራ በመስራታቸው ነው ብለዋል፡፡
የከተማዋን ሰላም ለማስጠበቅ ለምዕመናን የሰላም እሴቶችን በማስተማር የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን ነው ያሉት፡፡
ፓስተር ሮባ ካሳ በበኩላቸው፤ ልጆቻችን በስነ- ምግባር እንዲታነጹና ልዩነቶቻቸውን በውይይት የመፍታት ባህላቸውን እንዲያጎለብቱ እንሰራለን ብለዋል፡፡
ልጆቻችን በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲያድጉ እያስተማርን እንገኛለን ያሉት ደግሞ አባ ገዳ ወልደአብ ገብረአብ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ምክትል ሃላፊ ብርሃኑ ረታ በበኩላቸው፤ የሰላም እሴቶች ለአገርና ለትውልድ ግንባታ ያላቸው ፋይዳ የጎላ ነው ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማት እና የባህል መሪዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተሰሚነት በመጠቀም፣ የጋራ መግባባትን፣ መቻቻልንና ፍቅርን ማስረጽ እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።
ባለፉት ዓመታት ከህብረተሰቡ፣ ከሀይማኖት አባቶች፣ ከአገር ሽማግሌዎች፣ ከአባ ገዳዎችና ከሀደ ሲንቄዎች ጋር በተሰሩ ስራዎች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በዚህም የከተማዋን ሰላም አስተማማኝ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፤ በቀጣይም ከህብረተሰቡ ጋር የሚሰሩ የጸጥታ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ያረጋገጡት፡፡
ኮንፈረንሱ "የሰላም እሴትና መቻቻል ለአገርና ትውልድ ግንባታ ያለው ፋይዳ" በሚል መሪ ሀሳብ ነው የተካሔደው።