በማዕድን ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎች ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በተግባር እየታየ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በማዕድን ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎች ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በተግባር እየታየ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ የጀመረቻቸው ስራዎች ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው በተግባር እየታየ መሆኑን የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አራተኛውን ዓለም አቀፍ የማዕድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ (MINTEX Ethiopia 2025) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ከፍተዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ሀብታሙ ተገኝ (ኢ/ር) በዚሁ ወቅት፤ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማዕድን ዘርፍ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ዘርፉ የአገሪቷ የጀርባ አጥንት እየሆነ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል።
መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትልቅ ትኩረት ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
የተሰጠው ትኩረት ተከትሎ በርካታ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ኢንቨስት ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውንም አንስተዋል።
አገሪቷ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ በምታደርገው ጥረት የማዕድን ዘርፍን አስተዋጽኦ ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ሀብቶችን በአግባቡ ለመጠቀም መንግስት በትኩረት መስራት ከጀመረ ወዲህ ጥሩ ውጤት መመዝገቡን ተናግረዋል።
ባለሀብቱም በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርግም የተለያዩ ማበረታቻዎች እየተደረጉ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጪ ምንዛሬ የምታስገባውን የተፈጥሮ ጋዝ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ማምረት መጀመሯን አውስተዋል።
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውም በተሰራው ስራ ለውጥ እየታየ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የማዕድን ዘርፉን በአግባቡ በመጠቀም የአገሪቱን ብልጽግና እንዲረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።
ኤክስፖው የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በአንድ ላይ የሚያገናኝ በመሆኑ ለኢትዮጵያ ማዕድን ዘርፍ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ገልጸዋል።
አራተኛውን ዓለም አቀፍ የማዕድን እና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ (MINTEX Ethiopia 2025) ከዛሬ ህዳር 4 እስከ 7 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማእከል ይካሄዳል።