በማዕድን ልማት የተፈጠረው ከፍተኛ መነቃቃት በዘርፉ እመርታዊ ስኬት እንዲመዘገብ አስችሏል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
በማዕድን ልማት የተፈጠረው ከፍተኛ መነቃቃት በዘርፉ እመርታዊ ስኬት እንዲመዘገብ አስችሏል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦በማዕድን ልማት የተፈጠረው ከፍተኛ መነቃቃት በዘርፉ እመርታዊ ስኬት እንዲመዘገብ ማስቻሉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ አራተኛውን ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ (MINTEX Ethiopia 2025) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ከፍተዋል።
በኤክስፖው መክፈቻ ላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ የሀገር ውስጥና የውጭ አልሚዎች፣ ባለሀብቶች፣ ቴክኖሎጂ አምራቾች፣ የዘርፉ ምሁራንና አጋሮች ተገኘተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ መንግስት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው አምስቱ ብዝሃ ዘርፎች መካከል አንዱ ማዕድን ነው።
ኤክስፖው በማዕድን ዘርፍ ያሉትን መልካም ዕድሎች ከማሳየት ባሻገር በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችንና ፈተናዎችን በቅንጅት ለመፍታት ምክክር የሚደረግበት መሆኑን ተናግረዋል ፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ልዩ ልዩ ማዕድናት እንዳሏት ጠቅሰው፤ ይህም መጠን ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች የሚያስገኝ መሆኑን ገልጸዋል።
መንግሥት የማዕድን ዘርፉ ለኢኮኖሚ ዕድገት እና ለዜጎች ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲውል የሚያስችሉ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዱን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የማዕድን ዘርፉን ጨምሮ ለሌሎች ክፍለ ኢኮኖሚዎች ወሳኝ የሆኑ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን ከፍተኛ በጀት በመመደብ በመገንባት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና በሌሎችም የኃይል አማራጮች በመታገዝ የኃይል አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎችንና አሠራሮችን በመከተል ዘርፉ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን አስታውቀዋል፡፡
ከዘርፉ በሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በመታገዝ የዜጎችን ሕይወት በማሻሻል ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ማስረከብ እንችላለን ብለዋል።
በዘርፉ ያለውን ያልተነካ ዕምቅ አቅምና ለሁለንተናዊ ዕድገት ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጽኦ የሚፈትኑ ተግዳሮቶችን በተቀናጀ ፣ በተደራጀና በተናበበ መልኩ ለመፍታት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎና አጋርነት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ኤክስፖው ከዛሬ ጀምሮ እስከ ህዳር 7 ቀን 2018 ዓ.ም ለተከታታይ አራት ቀናት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማእከል ይካሄዳል።