ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ዋንጫ ቀሪ ስምንት ክለቦች ቀጣዩን ዙር ተቀላቅለዋል 

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዋንጫ የሁለተኛ ዙር መርሃ ግብር የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገዋል።

በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና አዳማ ከተማን 2 ለ 1 አሸንፏል።

አቡበከር አዳሙ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥሯል። አህመድ ሁሴን ለአዳማ ከተማ ብቸኛውን ጎል አስቆጥሯል።

ባህር ዳር ከተማ ሸገር ከተማን 2 ለ 0 አሸንፏል። በአዲስ አበባ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ አማኑኤል ገብረሚካኤል እና ግርማ ዲሳሳ የማሸነፊያ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ በሬድዋን ሸረፋ ግብ ሃዋሳ ከተማን 1 ለ 0 ረቷል።


 

በተመሳሳይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በመለያ ምት 4 ለ 2 አሸንፏል።

ሁለቱ ቡድኖች በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ያለ ምንም ግብ አቻ ተለያይተዋል።

በሌሎች ጨዋታዎች አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 2 ለ 1 እና ቢሾፍቱ ከተማ ደሴ ከተማን 1 ለ 0 ሲያሸንፉ ንብ እግር ኳስ ክለብ የካ ክፍለ ከተማን ደብረብርሃን ከተማ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማን በመለያ ምት ማሸነፍ ችለዋል።

ዛሬ እና ትናንት የተደረጉ ጨዋታዎችን ተከትሎ 16 ክለቦች ለሶስተኛው ዙር አልፈዋል።


 

ኢትዮጵያ መድን፣ ቤንች ማጂ ቡና፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ፣ አርባምንጭ ከተማ፣ ቦዲቲ ከተማ፣ መቀሌ 70 እንደርታ፣ መቻል፣ ነጌሌ አርሲ፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ፣ ደብረብርሃን ከተማ፣ ንብ እግር ኳስ ክለብ፣ ቢሾፍቱ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ሲዳማ ቡና 16ቱን የተቀላቀሉ ክለቦች ናቸው።

የወቅቱ የውድድሩ አሸናፊ ወላይታ ድቻ ከውድድሩ ተሰናብቷል።

የኢትዮጵያ ዋንጫ ሶስተኛ ዙር መርሃ ግብር በቀጣይ በሚገለጽ ቀን እና ቦታ ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም