ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል የምታስተዳድርበት ሥርዓት በአርዓያነት የሚታይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል የምታስተዳድርበት ሥርዓት በአርዓያነት የሚታይ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል የምታስተዳድርበት ሥርዓት በአህጉሪቷ አባል ሀገራት በአርዓያነት የሚታይ መሆኑን የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ ገለጹ።
አህጉራዊ የሰብዓዊ ጉዳዮችን በአፍሪካዊ መፍትሔ ምላሽ የመስጠት አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ በአፍሪካ ሕብረት የጤና፣ የሰብዓዊ ጉዳዮችና የማህበራዊ ልማት ኮሚሽን ገልጿል።
የአፍሪካ ሕብረት የስደት፣ ስደተኞችና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አምስተኛው የሚኒስትሮች መደበኛ ስብሰባ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በአምስተኛው የአፍሪካ ሕብረት የሚኒስትሮች መደበኛ ስብሰባም የአህጉሪቷን የሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ አሰጣጥ ሥርዓቶች ከውጭ ጥገኝነት በማላቀቅ በራስ አቅም መምራት እንደሚያስፈልግ ተመልክቷል።
የአህጉሪቷን አባል ሀገራትም ከተበታተነ የሰብዓዊ ድጋፍ ምላሽ አሰጣጥ አቅምን የሚያጎለብት ጠንካራ አፍሪካዊ መዋቅር መፍጠር እንደሚገባም ተገልጿል።
የፍትሕ ሚኒስትር ዴኤታ በላይሁን ይርጋ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በመቀበል የምታስተዳድርበት ሥርዓት በአህጉሪቷ አባል ሀገራት ጭምር በአርዓያነት የሚታይ ነው።
ኢትዮጵያ ስደተኞችን የምታስተዳድርበት ስኬታማ ሥርዓትም የአፍሪካ ሕብረት የስደት፣ ስደተኞችና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አህጉራዊ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢነት እንድትመረጥ እንዳስቻላት ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የስደት፣ ስደተኞችና የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች አምስተኛው የሚኒስትሮች መደበኛ ስብሰባም የአህጉሪቷን አባል ሀገራት ትብብር ለማጠናከር ወሳኝ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
የአፍሪካ ሕብረት የጤና፣ የሰብዓዊ ጉዳዮችና የማህበራዊ ልማት ኮሚሽነር አምባሳደር አማቱም-አሞአሃ በበኩላቸው፤ የአህጉሪቷን የስደት አስተዳደር የሚያዘምን ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል ብለዋል።
የአፍሪካን የስደት ተፅዕኖ የመቋቋም አህጉራዊ አቅም በመገንባት ተፅዕኖውን ወደ ልማት ዕድል መለወጥ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሰብዓዊ ምላሽ አህጉራዊ ሥርዓት ከውጭ ጥገኝነት የሚላቀቅበትን ምኅዳር በመፍጠር የአፍሪካን ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የመስጠት አጀንዳ 2063 ዓላማን ማሳካት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣናና የአህጉሪቷ ዜጎች ነፃ እንቅስቃሴ በአጀንዳ 2063 ላይ በቁልፍ አጀንዳነት የተቀመጠ መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነም አንስተዋል።
የዛምቢያ የውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር ቋሚ ጸሃፊ ዲክሰን ማቴምቦ፤ የአፍረካ ችግሮችን አፍሪካዊ መፍትሔ ለመስጠት የተቀመጠውን አጀንዳ 2063 ስኬት ትብብርን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
የአህጉሪቷን የስደት ተፅዕኖ ምላሽ የመስጠት አቅም ለመገንባትም የአፍሪካ የተቀናጀ ሰብዓዊ ድርጅት ለማቋቋም እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።