በሰው ኃይል ልማትና ክህሎት ማበልፀግ ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ትብብር አጠናክረን እንቀጥላለን -የልማት አጋሮች - ኢዜአ አማርኛ
በሰው ኃይል ልማትና ክህሎት ማበልፀግ ከኢትዮጵያ ጋር ያለንን ትብብር አጠናክረን እንቀጥላለን -የልማት አጋሮች
አዲስ አበባ፤ሕዳር 4/2018 (ኢዜአ)፡-በሰው ኃይል ልማትና ክህሎት ማበልፀግ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን ትብብር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የልማት አጋሮች ገለጹ፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በበኩሉ፥ ለቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ምቹ ሥነ-ምህዳር በመፍጠር ዘርፉ ለሀገር ብልፅግና የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ ለማጠናከር ከባለድርሻ አካላት ጋር ያለውን ትብብር እንደሚያጠናክር አስታውቋል።
ወጣቶች የተሻለ ዕውቀትና ክህሎት ታጥቀው የሥራ ገበያውን የሚቀላቀሉበትን አቅም የሚያሳድግ አዲስ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ይፋ ሆኗል።
ስትራቴጂው ከ2000 ዓ.ም ነባር ስትራቴጂ እና በ2015 ዓ.ም ስራ ላይ ከዋለው የትምህርት ስልጠና ፖሊሲ መልካም ተሞክሮዎች እንደተካተቱበት ተገልጿል።
አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ የክህሎት ተደራሽነትን በማስፋት ወጣቶች የተሻለ የስራ ዕድል የሚያገኙበትን ምቹ ምኅዳር ለመፍጠር ያለመ ነው ተብሏል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ፍትሃዊነትንና ተደራሽነትን በማስፋት የስልጠና ጥራትን ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና አለው።
የወጣቶችን የሥራ ፈጠራ፣ የሥራ ገበያ፣ የዲጂታል ዕውቀትና ክህሎትን በማጎልበት ሁሉንም አጣጥሞ መምራት በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ስትራቴጂ መሆኑን ገልጸዋል።
በስትራቴጂው ትግበራ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን ትብብር ማጠናከር ያስፈልጋልም ብለዋል፡፡
በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ የሚያሳልጥ በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል የማፍራት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት የሰው ሀብት ልማት ፕሮግራም ኦፊሰር ኢቫ ጁኒየት፤ ህብረቱ በኢትዮጵያ ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ የክህሎት ልማት መሆኑን ተናግረዋል።
የክህሎት ልማት ለስራ እድል ፈጠራ፣ ለኢንተርፕራይዝ ልማትና ለኢኖቬሽን ወሳኝ ሚና እንዳለው ጠቅሰው፤ አዲሱ ስትራቴጂ የግሉ ዘርፍና አጋር አካላት በትብብር እንዲሰሩ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሰው ሀብት ልማትን፣ ክህሎትንና እውቀትን ለማሳደግ ለምታከናውነው ጥረት ህብረቱ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ የጀርመን ኤምባሲ የልማት ትብብር አማካሪ አንጃ ፖልስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለልማት ወሳኝ የሆነ የሰው ሀብት አላት ብለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ለሀገራዊ ለእድገት፣ ምርታማነትን ለማሻሻልና አካታችነትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እንዳለው ተናግረዋል፡፡
ጀርመን በታዳሽ ኃይል፣ በግብርና፣ አየር ንብረት፣ በቴክኒክና ሙያ ስልጠናና ሌሎች ዘርፎች ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን በመጥቀስ፤ ያለንን የልማት አጋርነት አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል።
የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዲኖች ማህበር ፕሬዝዳንት መለሰ ግዛው፥ ስትራቴጂው የዘርፉን ችግር በመፍታት ቴክኒክና ሙያ ለኢትዮጵያ እድገት የሚያበረክተውን አስተዋፅኦ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል፡፡