የመንገድ መሠረተ ልማቶች በህብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት ሊጠበቁ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የመንገድ መሠረተ ልማቶች በህብረተሰቡ በባለቤትነት ስሜት ሊጠበቁ ይገባል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ በከፍተኛ ሃብት የሚገነቡ የመንገድ መሠረተ ልማቶችን ከምህንድስና ስሌት በላይ በህብረተሰብ የባለቤትነት ስሜት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር መሐመድ አብዱራህማን ገለጹ።
በኢትዮጵያ በከፍተኛ ወጪ የሚገነቡ የመንገድ መሠረተ ልማቶች የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ እያሳለጡ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
"ሀገርን በጥበብ" የኢዜአ ወርሃዊ የኪነ-ጥበብ መድረክ "ፍኖት ወደ ብልፅግና" በሚል መሪ ሀሳብ ተካሂዷል።
በመድረኩ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሚኒስትርና የኢዜአ የቦርድ ሰብሳቢ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሠይፈ ደርቤ፣ የኪነ-ጥበብ ሙያተኞችና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።
በኪነ-ጥበብ መድረኩ የተገኙት የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢነጂነር መሐመድ አብዱራህማን እንደገለጹት፤ ኪነ-ጥበብ የህዝብ ትክክለኛ ስሜትና ፍላጎት የሚንጸባረቅበት ስራ ነው።
የመንገድ ልማት ፕሮጀክት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት እንቅስቃሴ በወሳኝ መሳሪያነት የሚያገለግል መሠረተ ልማት ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።
የህብረተሰቡ የመንገድ ደኅንነት ጥበቃ ተሳትፎም የመሠረተ ልማት ዘላቂነትን ለማስጠበቅ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።
በከፍተኛ ወጪ የሚገነቡ መንገዶች የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ እያሳለጡ እንደሚገኝም አስረድተዋል።
የመንገድ መሠረተ ልማቶችን በዘላቂነት ለመጠቀም ህብረተሰቡ እንደራሱ ንብረት እንዲንከባከብ በጥበብ የተዋዛ የግንዛቤ የማስጨበጫ ሥራዎች ወሳኝ ናቸው ብለዋል።
በጥበብ መድረኩ የቀድሞ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የአሁኑ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር 75ኛ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ በመንገድ መሠረተ ልማት ጥበቃ ላይ ያተኮሩ የጥበብ ስራዎች ቀርበዋል።
የመንገድ መሠረተ ልማት ለኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ያለውን ፋይዳ የሚዘክሩ ጥበባዊ ሥራዎችም ቀርበዋል።