ቀጥታ፡

በክልሉ የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አብሮነትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል

ቦንጋ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን አብሮነትና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በሚያጠናክር መልኩ እንደሚከበር ተገለጸ።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የብሔረሰቦች ምክር ቤት 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀንን በማስመልከት በቦንጋ ከተማ የአሰልጣኞች ስልጠና እየሰጠ ነው።

በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤና የበዓሉ ዝግጅት አብይ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ወንድሙ ኩርታ እንደገለጹት፣ በክልሉ ቀኑን በተለየ መልኩ በድምቀት ለማክበር ሰፊ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።


 

የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በክልል ደረጃ በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን ከተማ በአደባባይ እንደሚከበር ጠቁመው፣ በዓሉ ከትምህርት ቤት ጀምሮ ከወዲሁ በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በማጠቃለያውም የደም ልገሳና የአረጋውያን ቤት ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ በጎ ተግባራት እንደሚከናወኑ አመልክተዋል።


 

የክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤና የበዓሉ ዝግጅት አብይ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጌታቸው ኬኒ በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ሲከበር ለብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች አንድነትና ግንኙነት እንዲሁም ወንድማማችነት እየተጠናከረ እንዲመጣ ትኩረት መሰጠቱን አመልክተዋል።

በዓሉን በየደረጃው በሚገኙ መዋቅሮች በተሻለና በደመቀ መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ "ዴሞክራሲ እና የፌደራል ስርዓት በኢትዮጵያ፤ ተስፋዎቹና ተግዳሮቶቹ" የሚል ሰነድ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ይገኛል።

የዘንድሮ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እንደሚከበር ቀደም ሲል መገለጹ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም