ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የማዕድን ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃትና እመርታ እያስመዘገበ ይገኛል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ - ኢዜአ አማርኛ
ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የማዕድን ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃትና እመርታ እያስመዘገበ ይገኛል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ ለማዕድን ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃትና እመርታ እያስመዘገበ መምጣቱን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለፁ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አራተኛውን ዓለም አቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ (MINTEX Ethiopia 2025) በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ከፍተዋል።
የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የዘርፉ የሀገር ውስጥና የውጭ አልሚዎች፣ ባለሀብቶች፣ ቴክኖሎጂ አምራቾች፣ የዘርፉ ምሁራንና አጋሮች የሚሳተፉበት ነው።
መንግስት ልዩ ትኩረት ከሰጣቸው ከአምስቱ ብዝሃ ዘርፎች መካከል አንዱ ማዕድን መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰዋል።
ኤክስፖ በማዕድን ዘርፍ ያሉትን መልካም ዕድሎች ከማሳየት ባሻገር በዘርፉ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችንና ፈተናዎችን በቅንጅት ለመፍታት ምክክር የሚደረግበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ልዩ ልዩ ማዕድናት ባለጸጋ መሆኗን ጠቅሰው፤ ይህም መጠነ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድሎች እንዳሉ አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የማዕድን ዘርፉ ለሀገራችን ኢኮኖሚ ዕድገትና ለዜጎች ሁለንተናዊ ብልጽግና እንዲውል የሚያስችሉ እርምጃዎች መውሰዱን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ለማዕድን ዘርፍ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ክፍለ ኢኮኖሚዎች ወሳኝ የሆኑትን የተለያዩ የመሠረተ ልማት ዝርጋታዎችን፣ ከፍተኛ በጀት በመመደብ በመገንባት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እና በሌሎች የኃይል አማራጮች አማካኝነት የኃይል አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዓለም አቀፋዊ ምርጥ ተሞክሮዎችንና አሠራሮችን በመከተል የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማታችን ለኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን አስተዋጽዖ ከማበርከት ባለፈ የዜጎች ሕይወት እንዲሻሻል በማድረግ ለመጪው ትውልድ የተሻለች ሀገር ማስረከብ እንችላለንም ነው ያሉት።
የማዕድን ዘርፉ ያለውን ያልተነካ ዕምቅ አቅም ለሀገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጽዖ እንዳይወጣ የሚያደርጉ ተግዳሮቶችን በተቀናጀ፣ በተደራጀና በተናበበ መልኩ ለመፍታት የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ወሳኝ ተሳትፎና አጋርነት ይጠይቃል ብለዋል።
ኤክስፖው ከዛሬ ህዳር 4 እስከ 7 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ይካሄዳል።