በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ የሰው ሀይል በማፍራት የኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ ማሳለጥ ያሰፈልጋል - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል - ኢዜአ አማርኛ
በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ የሰው ሀይል በማፍራት የኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ ማሳለጥ ያሰፈልጋል - ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ በዕውቀትና ክህሎት የበለጸገ የሰው ሀይል በማፍራት የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የዕድገት ጉዞ ማሳለጥ እንደሚያስፈልግ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
ወጣቶች የተሻለ ዕውቀትና ክህሎት ታጥቀው የሥራ ገበያውን የሚቀላቀሉበትን አቅም የሚያሳድግ አዲስ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ይፋ ሆኗል።
የስትራቴጂ ዝግጅትም ከ2000 ዓ.ም ነባር ስትራቴጂ እና በ2015 ዓ.ም ስራ ላይ ከዋለው የትምህርት ስልጠና ፖሊሲ ላይ መልካም ተሞክሮዎች እንደተካተቱበት ተገልጿል።
አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂም የክህሎት ተደራሽነትን በማስፋት ወጣቶች የተሻለ የስራ ዕድል የሚያገኙበት ምቹ ምኅዳር ለመፍጠር አልሟል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ አዲሱ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ስትራቴጂ ፍትሕዊነትና ተደራሸነትን በማስፋት የስልጠና ጥራትን ለማስጠበቅ ወሳኝ ሚና አለው።
የስልጠና ጥራትና ተገቢነትን በማስጠበቅ ወጣቶችን ገበያው የሚፈልገውን ዕውቀትና ክህሎት በማስታጠቅ ጉልህ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።
አዲሱ ስትራቴጂም የወጣቶችን የሥራ ፈጠራና የሥራ ገበያ የዲጂታል ዕውቀትና ክህሎት አቅምን በማጎልበት አጣጥሞ መምራት በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።
የቴክኒክና ሙያ የስልጠና ኮሌጆች የስራ ገበያ ኢንዱስትሪው የሚፈልገውን የሰው ሀይል በዘላቂነት ማፍራት የሚችሉበትን ምኅዳር ለመፍጠር እንደሚረዳም ተናግረዋል።
በአዲሱ ስትራቴጂ ትግበራ ሂደትም የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመንግስትና የግሉ ዘርፍ ባለድርሻ አካላትን ትብብር ማጠናከር እንደሚያስፈለግ አስገንዝበዋል።
የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት የኢትዮጵያን የዕድገት ጉዞ የሚያሳልጥ በዕውቀትና ክህሎት የዳበረ የሰው ሃይል የማፍራት ስራም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከክልሎችና ከግል ዘርፉ እንዲሁም ከዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ይህ ስትራቴጂ የኢትዮጵያን የቴክኒክና የሙያ ስልጠና ስርዓት ጥራት የሚያሻሽል መሆኑም ተመላክቷል።