በሰሜን ሽዋ ዞን የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን የመከላከል ተግባር እያከናወንን እንገኛለን - አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
በሰሜን ሽዋ ዞን የደረሱ ሰብሎችን ፈጥኖ በመሰብሰብ የምርት ብክነትን የመከላከል ተግባር እያከናወንን እንገኛለን - አርሶ አደሮች
ደብረ ብርሃን/ምዕራብ ጎንደር፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን የደረሱ ሰብሎችን ፈጥነው በመሰብሰብ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ የሚከሰት የምርት ብክነትን የመከላከል ተግባር እያከናወኑ እንደሚገኙ የመርሐቤቴ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ።
በዞኑ በመኸር ወቅቱ ከለማው ሰብል ውስጥ 159ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል መሰብሰቡ ተገልጿል።
በመርሐቤቴ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ዳምጠው ተሾመ ለኢዜአ እንዳሉት በመኸር ወቅቱ ከ5 ሄክታር በላይ መሬትን በጤፍና በማሽላ ሰብል ማልማት ችለዋል።
በባለሙያዎች ክትትልና ድጋፍ በመታገዝም ያለሙትን የጤፍ ሰብል በደቦ መሰብሰባቸውን ተናግረዋል።
አርሶ አደር ከፈለ ደጀን በበኩላቸው በመኸር ወቅት ሦስት ሄክታር የሚጠጋ ማሳቸውን በጤፍና በማሽላ ሰብል ማልማታቸውን ጠቁመው የደረሰውን የጤፍ ሰብላቸውን ወቅቱን ካልጠበቀ ዝናብ ለመከላከል ቀድመው እየሰበሰቡ እንደሚገኙ አንስተዋል።
የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አበበ ጌታቸው በበኩላቸው በዚህ የመኸር ወቅት 563ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ማልማት ተችሏል።
ቀድመው የደረሱ ሰብሎችን በፍጥነት ለመሰብሰብ በተደረገ ጥረትም 159ሺህ 395 ሄክታር መሬት ምርትን በመሰብሰብ 780ሺህ 576 ኩንታል ምርት መገኘቱን ጠቅሰው፤ ቀሪውን የሰብል ምርት በፍጥነት እየተሰበሰበ መሆኑን ተናግረዋል።
በተመሳሳይም በክልሉ ምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር የለሙ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች ሰብሎችን ለመሰብሰብ ከ300ሺህ በላይ ለሚሆኑ የጉልበት ሠራተኞች የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል።
የመምሪያው ኃላፊ ኤፍሬም ወርቁ ለኢዜአ እንደገለጹት ዞኑ ሰፋፊ መሬትና ለወጭ ንግድ ተስማሚ የአየር ንብረት ያለው በመሆኑ በሜካናይዜሽን የታገዘ የሰብል ልማት የሚካሄድበት ነው።
የዞኑ ወረዳዎች በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሃብቶችና አርሶ አደሮች ለወጪ ንግድ፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለምግብ ፍጆታ የሚውሉ ሰብሎችን በብዛት የሚመረቱባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን በ2017/2018 የምርት ዘመን በሰብል ከለማው ከ529 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከ12 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚሰበሰብ ከመምሪያው የተገኘው መረጃ ያመላክታል።