ቀጥታ፡

የግጭትና አለመግባባት ምክንያቶችን በምክክር በመፍታት ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት በጋራ መትጋት ይገባል

አርባ ምንጭ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ የግጭትና አለመግባባት ምክንያቶችን በምክክር በመፍታት ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት በጋራ መትጋት ይገባል ሲል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ገለጸ።

"ኃይማኖቶች ለሰላም፣ ለአንድነትና ለአብሮነት" በሚል መሪ ሃሳብ በአርባ ምንጭ ከተማ ለሁለት ቀናት የተካሄደው 5ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ ተጠናቋል።

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀኃፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ፤ የአብሮነት፣ የመተባበርና የመከባበር እሴቶች የኢትዮጵያውያን የቆዩና አሁንም የዘለቁ ሃብቶች ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም የብዝሃነት ተምሳሌት የሆነችውን ሀገር እሴቷን በመጠበቅና ሀገራዊ አንድነትና ትብብርን በማጠናከር ለቀጣዩ ትውልድ የተሻለች ሀገር ማስረከብ የሁላችንም አደራና ሃላፊነት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይም የሃይማኖት ተቋማት በሰላም ግንባታ ላይ በመስራት፣ መልካምነትን በማስተማርና ለሀገር እድገት የዜጎች ተሳትፎ እንዲጠናከር የማስተማር ሃላፊነት ያለባቸው መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም የግጭትና አለመግባባት ምክንያቶችን በምክክርና በመግባባት ከመሰረቱ በመፍታት ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ብሔራዊ መግባባት መትጋት ይገባናል ብለዋል።

የሀገርን ሰላም ለማናጋትና በዜጎች ዘንድ ስጋትና ጥርጣሬ ለመፍጠር የሚሰሩ ግለሰቦች ከጥፋት እንቅስቃሴያቸው እንዲታቀቡም ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ጠይቀዋል።

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ከይሬድን ተዘራ (ዶ/ር) የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥና የሀገርን እድገትና ብልጽግና እውን ለማድርግ በተለያዩ መስኮች የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ትልቅ ተስፋ የተሰነቀባቸው መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ፕሮጀክቶች ለስኬት እንዲበቁ በሁሉም አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት መፍጠር፣ በልማትና የሀገር ግንባታ ሂደት የነቃ ተሳትፎ ማድረግና ለተግባራዊነቱ መትጋት የሁላችንም ሚና ሊሆን ይገባል ብለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ፤ የሰላም ጉዳይ የሁሉ ነገር መሰረት በመሆኑ በመከባበር፣ በመተባበርና በመተጋገዝ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለሀገር እድገትና ብልጽግና መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል።

የሰላም ግንባታ ከፍላጎትን ባለፈ ተግባራዊ እንቅስቃሴን የሚጠይቅ በመሆኑ በዚህ ረገድ የሃይማኖት ተቋማት የላቀ ሚናቸውን እንዲወጡም ጠይቀዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሃይማኖት ፎረም ሰብሳቢ ቀሲስ መላከሰላም ቦኪቻ፤ ከሰላም ትሩፋቶች ተጠቃሚ ለመሆን ሁሉም በያለበት የሰላም አምባሳደር መሆን አለበት ብለዋል።

ለተከታታይ ሁለት ቀናት በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደው ኮንፈረንስ ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የሃይማኖት ጉባኤ አባላት፣ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም