ቀጥታ፡

የብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በክልሉ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል - አፈ ጉባኤ አያን አብዲ

ጅግጅጋ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ 20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የሶማሌ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አያን አብዲ አስታወቁ።

የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አያን አብዲ 20ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አከባበር አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ ቀኑ በክልሉ ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጠናክሩ ልዩ ልዩ ሁነቶችና የልማት ተግባራት ይከበራል።

በመርሃ ግብሮቹ ህብረ ብሔራዊነትን ማጠናከር በሚያስችሉ ተግባራትና የአንድነት እሴቶችን የሚያጎለበቱ ሁነቶች እንደሚከናወኑም ገልጸዋል።

በክልሉ ደረጃ ህዳር 17 ቀን 2018ዓ.ም እንደሚከበር ጠቅሰው ከህዳር 5 ቀን 2018ዓ.ም ጀምሮ በሁሉም የክልሉ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በህገ መንግስቱ ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጡና አንድነትን የሚያጠናክሩ ውይይቶች፣ የልማት እንቅስቀሴዎች እንዲሁም የበጎ ፈቃድ ስራዎች ይካሄዳሉ ብለዋል።

20ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ''ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኀብረብሔራዊ አንድነት'' በሚል መሪ ሀሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም