በዞኑ የማር ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ተግባር ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር በማስተሳሰር እየተከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የማር ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ተግባር ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር በማስተሳሰር እየተከናወነ ነው
ጭሮ፤ ህዳር 4/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሐረርጌ ዞን የማር ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ተግባር ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር በማስተሳሰር እየተከናወነ መሆኑን የዞኑ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ ዶክተር ፋሩቅ አሊዪ ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ የማር ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል ተግባር ከተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ጋር በማስተሳሰር የአርሶ አደሩን የገቢ አማራጭ ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በዚህም ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ የልማት ስራዎች እየጨመረ የመጣውን የደን ልማት በመጠቀም በማር ምርት እንዲሰማሩ በበጀት ዓመቱ ከ16 ሺህ በላይ ዘመናዊ ቀፎዎችን ለአርሶ አደሮች ለማከፋፈል መታቀዱን ገልጸዋል።
እስካሁንም ከ12ሺ በላይ የሚሆነው መከፋፈሉን አመልክተው በልማቱ ለተሰማሩትም ድጋፍና ክትትል በማድረግ ከ3 ሺህ 600 ቶን በላይ ምርት ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በገመቺስ ወረዳ መደራ ቀበሌ አርሶ አደር ጀማል አህመድ እንዳሉት ባለፈው ዓመት ባገኙት ሰባት ዘመናዊ ቀፎ ለመጀመርያ ጊዜ በንብ ማነብ ስራ ላይ ተሰማርተዋል፡፡
የማር ምርታቸውን ለማሳደግም በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተተከሉ ችግኞች ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከመንግስት ባገኙት ዘመናዊ ቀፎ በንብ ማነብ ስራ ላይ ተሰማርተው ለመጀመርያ ጊዜ ምርት ለመሰብሰብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ቶፊቅ አብዱረህማን ናቸው፡፡
በባለሙያዎች በመታገዝ የንብ ማነብ እና የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዉን በቅንጅት በማከናወን ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ እና የንብ ማነብ ስራ ተያያዥነት እንዳላቸው በመረዳታቸው ልማቱን በቅንጅት ለማከናወን በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን 15 ወረዳዎች በአሁኑ ወቅት ከ47 ሺህ 600 በላይ የቤተሰብ መሪዎች በንብ ማነብ ስራ ላይ ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ከዞኑ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡