ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የብሔራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ ባሻገር የቀጣናዊ ደኅንነት መሠረታዊ ጉዳይ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የብሔራዊ ጥቅምን ከማስጠበቅ ባሻገር ለቀጣናዊ ደኅንነት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ከፍተኛ አመራር ቀጀላ መርዳሳ ገለጹ።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነትን እንድታጣ የተደረገበት መንገድ ሕጋዊ መሰረት የሌለው በሀገር ላይ የተፈጸመ በደል መሆኑንም ተናግረዋል።

ቀይ ባሕር ምዕተ ዓመታትን በተሻገረ ዘመን የኢትዮጵያ የንግድና የሥልጣኔ ማዕከል ሆኖ ማገልገሉን የታሪክ መዛግብትና ጸሐፍት የከተቡት የትውልዶች ሐቅ መሆኑ ይታወቃል።

ከጥንተ የአክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮም ቀይ ባሕር የኢትዮጵያና ዜጎቿ የገናና ታሪክ መገለጫና የታላቅነት ሕያው ምስክር የተፈጥሮ ወሰን በመሆን ጭምር ማገልገሉን የታሪክ ሰነዶች ያረጋግጣሉ።

ከ1983 ዓ.ም ወዲህ የወቅቱ የኢትዮጵያ አስተዳደር ማስረጃ ባልተገኘለት አኳኋን ኢትዮጵያ ለሺህ ዓመታት ከነበረችበት የቀይ ባሕር ቀጣና ውሉ በማይታወቅ የፖለቲካ ሴራ እንድትገፋ ሆኗል።

የስልጣኔ መነሻ፣ የንግድ ግንኙነት ማዕከል፣ የተፈጥሯዊና ሕጋዊ ወሰን ከሆነው ቀይ ባሕር የተገፋችበት የታሪክ ስብራትም በዜጎቿ ላይ የኢኮኖሚ ዕድገት እንቅፋትና የጂኦ-ፖለቲካ ስጋት ደቅኖ ቆይቷል።

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ከፍተኛ አመራር ቀጀላ መርዳሳ፤ በአንድ ጥላ ስር የነበሩት የኢትዮጵያና ኤርትራ ህዝቦች በታሪካዊ ጠላቶች በተሸረበ ሴራ በሁለት ሀገርነት ስም እንዲነጣጠሉ መደርጉን አስታውሰዋል።

ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተነጠለችበት ኢ-ፍትሕዊ እና ፍርደ ገምድል ውሳኔም ኢትዮጵያን ከቀይ ባሕር ቀጠና የመግፋት ታሪካዊ የፖለቲካ ሴራ ውጤት መሆኑንም የታሪክ ድርሳናትን በማጣቀስ ቅቡልነት የሌለው ተግባር እንደነበር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት እንድታጣ የተደረገበት መንገድ ሕጋዊ መሰረት የሌለው በሀገር ላይ የተፈጸመ በደል መሆኑንም አቶ ቀጀላ አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ አካል የነበረው የአሰብ ወደብና አካባቢ ከአስመራ ከ500 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ የሚገኝ ለኢትዮጵያ ቅርብ የሆነ አካባቢ መሆኑንም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ከተገነቡ መሠረተ ልማቶች ውጭ የአሰብ አካባቢ ያለአንዳች የልማት እንቅስቀሴ ቆሞ ማየትም የሚያስቆጭ ጉዳይ እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ የብሔራዊ ጥቅምን የማስጠበቅ የቀጣናዊ ደኅንነት መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑንም ነው ጨምረው የተናገሩት።

የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚያሳልጥ ሰላማዊና በሰጥቶ መቀበል መርህ የተመሰረተውን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄም አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም