ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለቀጣናው ሀገራት ሰላምና መረጋጋት የጎላ አበርክቶ ይኖረዋል - አምባሳደር ዘሪሁን አበበ

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ለቀጣናው ሀገራት ሰላምና መረጋጋት የጎላ አበርክቶ እንዳለው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን ሁለተኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት የቀይ ባህር ጉዳይ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ መሆኑን ማንሳታቸው ይታወቃል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በሕዝብ ብዛት፣ በወታደራዊ ኃይል፣ በኢኮኖሚ የቀጣናው ትልቅ ሀገር ናት፡፡

ኢትዮጵያ ከስድስት ሀገራት ጋር ድንበር እንደምትጋራ በመግለጽ፤ በታሪክና በጂኦግራፊ የቀጣናው መልህቅ መሆኗንም ገልጸዋል፡፡

ከጎረቤት ሀገራት ጋር በሕዝብ፣ በተፈጥሮ ኃብትና መሰረተ ልማት የተሳሰረች መሆኗን በማንሳት፤ ኢትዮጵያ ብቻዋን ብታድግ ግንጥል ጌጥ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ስታድግ ቀጣናውም ያድጋል የሚል እሳቤ እንከተላለን ያሉት አምባሳደሩ፤ የቀጣናው ሰላምና መረጋጋት የኢትዮጵያም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በቀጣናው ሰላም አስከባሪ ኃይል ማሰማራት፣ የሱዳን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እንዲቆም የመታደርገው ጥረት በኢጋድ፣ በአፍሪካ ሕብረትና በዓለም አቀፍ ባለብዙ ወገን መድረኮች ለትብብር ያላትን ሚና የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡

የመደመር ፍልስፍና ከቀጣናው ሀገራት ጋር መግባባትና ትብብር በመፍጠር ያለንን በማካፈልና በመካፈል ግብን መሳካት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ፣ ድንበር ተሻጋሪ ኃብቶችን በጋራ የመጠቀም ፍላጎት፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ በጋራ የመልማት ፍላጎቷ ማሳያዎች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ለቀጣናው ሀገራት ሰላምና መረጋጋት የጎላ አበርክቶ እንዳለው ያነሱት አምባሳደር ዘሪሁን፤ ይህም ለቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ያላትን መሻት ያረጋግጣሉ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ ቀጣናዊ ብልጽግናን የማረጋገጥ ህልሟን ለማሳካት የባህር በር ባለቤትነትን ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም