ቀጥታ፡

የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክን ብዝሃ ህይወት በመጠበቅ ስነ-ምህዳራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳውን ለማጎልበት ትኩረት ተሰጥቷል

ወልቂጤ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ ብዝሃ ህይወትን በመጠበቅ ስነ-ምህዳራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳውን ለማጎልበት ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኘው የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ በሀገሪቱ ከሚገኙ ፓርኮች አንዱ ነው።

የጊቤ ሸለቆ ብሔራዊ ፓርክ በውስጡ በርካታ የዱር አንስሳት፣ አዕዋፋት፣ የውሀ ውስጥ እንስሳትና የተፈጥሮ ዛፎችን የያዘ ነው።

የፓርኩ ጠቅላላ የቆዳ ስፋት 360 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍንና በውስጡ ከ20 በላይ የዱር እንስሳት ሲኖሩ ከእነዚህም መካከል አጋዘን፣ ጉማሬ፣ ነብር፣ ጉሬዛ፣ ከርከሮ፣ አቦ ሸማኔና ድኩላ ተጠቃሽ ናቸው።

እስካሁን በተደረገ ጥናት በፓርኩ ከሚገኙ አዕዋፋት መካከል ነጭ የቋጥኝ ወፍ፣ ጋጋኖ፣ የሀሩስድ ቆቅ የመሳሰሉት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ።

ከውሃ ውስጥ እንስሳትም አዞ፣ ጉማሬ፣ እንዲሁም ከአምስት በላይ የዓሳ ዝርያዎች ይገኙበታል።

የተንጣለለው የፓርኩ ቦታም በበርካታ እድሜ ጠገብ ዛፎችና ሌሎች በመካከለኛና አነስተኛ ቁጥቋጦና የሳር ዝርያዎች የተሸፈነ ነው።

በፓርኩ ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ወንዞች ዶባ መቅደላ መንደር፣ ሉቆ ሲቆራ፣ ናይካም ወንዝ፣ እንዲሁም ናይካም ፏፏቴ፣ ቋሽቋሽ ፏፏቴ፣ ጃቱ ፍል ውሃ፣ ሉቄ ፍል ውሃ እንዲሁም ጓንታና እና ሄሬሪኬ ዋሻ ተጠቃሽ ናቸው።

የፓርኩ ስራ አስኪያጅ መስፍን ተካ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የፓርኩን ብዝሃ ህይወት በመጠበቅ ስነ-ምህዳራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳውን ለማጎልበት እየተሰራ ይገኛል።

በዚህም የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር እየጨመረ ከመምጣቱም ባለፈ የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህልና እሴት እንዲተዋወቅ ማገዙን ተናግረዋል።

ፓርኩ ባለፈው በጀት ዓመት ከ13ሺህ በላይ በሚሆኑ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች መጎብኘቱንና ከ850 ሺህ ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አውስተዋል።

የጎብኚዎችን ቁጥር ለማሳደግ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የማስተዋወቅ እና ቆይታቸውን ማራዘም የሚያስችሉ መሰረተ ልማት እየተዘረጋ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ፓርኩ በተፈጥሮ የታደለ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በተለያየ ጊዜ ፓርኩን የጎበኙትና የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት ብሩክ ደሊል ናቸው።

በፓርኩ የሚገኙ ዕድሜ ጠገብ ዛፎችና ልዩ ልዩ ዕፅዋት ለጎብኚዎች ከሚፈጥሩት ሀሴት በተጨማሪ አዞዎችና ጉማሬዎች በውሃ ውስጥ የሚያደርጉት ትዕይንት እጅግ ማራኪ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ አቅጣጫዎች ወደ ፓርኩ ሲገባ የአካባቢው ነዋሪ ባህላዊ እሴትን የሚያንጸባርቁ መንደሮች፣ ፏፏቴዎችና የፍልውሃ ቦታዎች ለፓርኩ የተለየ ገጽታ እንዳላበሱትም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም