በምስራቅ ኢትዮጵያ የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ በነበረው አሸባሪው ሸኔ ላይ እርምጃ ተወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ኢትዮጵያ የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ በነበረው አሸባሪው ሸኔ ላይ እርምጃ ተወሰደ
ሐረር ፤ ሕዳር 4/2018 (ኢዜአ)፡- በምስራቅ ኢትዮጵያ የተወሰኑ አካባቢዎች የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሲንቀሳቀስ በነበረው አሸባሪው ሸኔ ላይ እርምጃ መውሰዱን በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ እዝ አስታወቀ።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የምስራቅ ዕዝ መሀንዲስ መምሪያ ሃላፊ ኮሎኔል ተፈሪ ኦሊ፤ አሸባሪው ሸኔ በድሬዳዋና አካባቢው የሽብር ተግባር ለመፈፀም ሙከራ ማድረጉን በማስታወስ ለኢዜአ ገልጸዋል።
በመሆኑም የአሸባሪውን የጥፋት ዓላማ እና እንቅስቃሴ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ጥናትና ክትትል በማድረግ ቀድሞ በመረዳት ወደ እርምጃ መገባቱን አስረድተዋል።
የመከላከያ ሰራዊት ከተለያዩ የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት በሽብር ቡድኑ ላይ ጠንካራ እርምጃ መወሰዱን አስታውሰው፤ በአካባቢው አሁን ላይ አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን አረጋግጠዋል።
በወታደራዊ እርምጃው ከጸጥታ አካላትም ባለፈ የአካባቢው ማህበረሰብ ትብብርና ተሳትፎ የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የልማት ስራዎች በስኬት እንዲቀጥሉ እንዲሁም ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር ሰራዊቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ በላቀ ዝግጁነት ተልዕኮውን በብቃት እየተወጣ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።
የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ናስር መሀመድ፤ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት በማረጋገጥ ሂደት የተደረገው ቅንጅታዊ ጥረት የሚፈለገውን ውጤት አምጥቷል ብለዋል።
በተለይም በዞኑ ለጥፋት ተግባር በተንቀሳቀሰው አሸባሪው ሸኔ ላይ በተወሰደው እርምጃ የተሳካ ውጤት መገኘቱን ተናግረዋል።