በደም እጥረት ምክንያት የሚከሰት የዜጎችን ሞት ለማስቀረት የደም ልገሳ ተግባራችንን እናጠናክራለን--የሮቤ ከተማ ደም ለጋሾች - ኢዜአ አማርኛ
በደም እጥረት ምክንያት የሚከሰት የዜጎችን ሞት ለማስቀረት የደም ልገሳ ተግባራችንን እናጠናክራለን--የሮቤ ከተማ ደም ለጋሾች
ሮቤ፤ ህዳር 4/2018 (ኢዜአ)፦ በደም እጥረት ምክንያት የሚከሰት የዜጎችን ሞት ለማስቀረት የበጎ ፈቃድ ደም ልገሳ ተግባራቸውን እንደሚያጠናክሩ በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ በጎ ፍቃደኛ ደም ለጋሾች ተናገሩ።
የጎባ ደም ባንክ በበኩሉ የለጋሾችን ቁጥር በማሳደግ የደም አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቋ፡፡
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾች መካከል ለ52ኛ ጊዜ ደም የለገሱት አቶ ታደሰ ታሪኩ አንዱ ናቸው።
በተደጋጋሚ በለገሱት ደም የሌሎችን ሕይወት ከመታደግ ባለፈ የራሳቸውን ጤንነት ለመጠበቅ በማገዙ የህልናን እርካታ እንዳገኙ ተናግረዋል።
በቀጣይም የጀመሩትን የደም ልገሳ ተግባር ሌሎችንም በማስተባበር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው የገለጹት።
"ደም መለገስ ህይወትን ከመታደግ ባሻገር ለራስም የሂሊና እርካታን ያስገኛል" ያሉት ደግሞ ለ32ኛ ዙር ደማቸውን የለገሱት በጎ ፍቃደኛ አቶ ሙላቱ ወቅሹሜ ናቸው።
በበጎ ፈቃድ ተግባሩ ከመሳተፍ ባሻገር ልምዳቸውን ለሌሎች በማስተማር ባለፈው ዓመት ብቻ በእሳቸው አስተባባሪነት ከ100 በላይ በጎ ፍቃደኞች ደም እንዲለግሱ ማድረጋቸውን አስታውሰዋል።
የጀመሩትን የደም ልገሳ ወደፊትም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው በደም እጦት ምክንያት በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሞት ለመታደግ ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የሮቤ ከተማ ትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሾላዬ ተገኔ በበኩላቸው በከተማ አስተዳደሩ በሚገኙ ሁሉም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተቋቋሙ ክለቦች በደም ልገሳና ሌሎች በጎ ተግባራት ውስጥ እየተሳተፉና ለማህበረሰቡም ግንዛቤ እየፈጠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የጎባ ደም ባንክ ዳሬክተር አቶ ሙሉ በቀለ በበኩላቸው በደም እጦት ምክንያት የሚከሰተውን የዜጎች ሞት ለመታደግ ዘንድሮ 8ሺህ ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ተናግረዋል።
ከዚህ ውስጥ በመጀመሪያው ሩብ ዓመት 2ሺህ 500 ዩኒት ደም ለመሰብሰብ ተችሏል ብለዋል።
የደም ለጋሾችን ቁጥር ለማሳደግ በትምህርት ቤቶችና በተለያዩ ህዝባዊ መድረኮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በመሰራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀሪ ወራት ህብረተሰቡን በማስተባበር በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ በዕቅድ የተያዘውን 8ሺህ ዩነት ደም ለማሳካት ባለድርሻ አካላት አስተዋጿቸውን እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል።