ቀጥታ፡

ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ጉባዔ የንግድና ኢንቨስትመንት እምቅ አቅምን ለዓለም ለማሳየት መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦14ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ጉባዔ የኢትዮጵያን የንግድና ኢንቨስትመንት እምቅ አቅም ለዓለም ለማሳየት መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

14ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ጉባዔ "የእሴት ሰንሰለቶችን በማጠናከር ዓለም አቀፍ የመዳረሻ ገበያዎችን ማስፋት" በሚል መሪ ሀሳብ ህዳር 9 እና 10 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር ጉባዔውን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የንግድ ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ አብዱልሀኪም ሙሉ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በ14ኛው የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ጉባዔ ላይ በዘርፉ የተሰማሩ ከ600 በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ተሳታፊዎች ይታደማሉ፡፡

ጉባኤው ኢትዮጵያ በዘርፉ ያላትን እምቅ አቅም በማስተዋወቅ የገበያ መዳረሻዎችን ለማስፋት የሚያግዝ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በአምራቾች፣ ላኪዎችና ባለድርሻ አካላት መካከል የገበያ ትስስር መፍጠር እንደሚያስችል ገልጸው፤ ኢትዮጵያ የንግድና ገበያ ዕድሎቿን በማስተዋወቅ ኢንቨስትመንትን መሳብ ያስችላል ብለዋል፡፡

በጥራጥሬና ቅባት እህሎች እሴት ሰንሰለት በሚስተዋሉ ችግሮች ዙሪያ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማፈላለግ የሚመክር ጉባኤ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይሄውም በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ መካከል ያለውን ትስስር ለማጠናከር ያግዛል ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ ለውጡን ተከትሎ የተደረጉ የፖሊሲ ሪፎርምና ሕግ ማሻሻያዎች ከወጪ ንግድ የሚገኘውን ገቢ እያሳደገው መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በ2017 በጀት ዓመት የተገኘው ስምንት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ከ2016 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ4 ነጥብ 59 ቢሊዮን ዶላር ብልጫ አለው ብለዋል።

በ2018 በጀት ዓመትም ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች ዘጠኝ ነጥብ አራት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት መታቀዱን በማንሳት፤ ዓለም አቀፉ የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ጉባኤ ለግቡ መሳካት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ላኪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ኤዳኦ አብዲ በበኩላቸው፤ የአሜሪካ፣ አውሮፓና እስያ ጨምሮ ከተለያዩ ሀገራት ተሳታፊዎች እንደሚመጡ ተናግረዋል።


 

በጉባኤው ላይ በርካታ ገዥ ሀገራት የሚሳተፉ መሆኑን አመልክተው፤ የኢትዮጵያን ምርቶች ለዓለም ለማስተዋወቅ መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ልምድ ካላቸው ሀገራት ተሞክሮ የምትቀስምበት መርሃ ግብር መሰናዳቱን ገልጸው፤ ጉባኤው ግቡን እንዲመታ አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ መመዘኛዎችን ያሟሉ ጥራት ያላቸው ምርቶችን የምታረጋግጥበት የጥራት መንደር በተሳታፊዎች እንዲጎበኝ መርሃ ግብር እንደተያዘለትም ተናግረዋል፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው ጉባዔ የሀገር ውስጥ አምራቾች፣ ላኪዎች፣ ዓለም አቀፍ ገዥዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ ዲፕሎማቶችና ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም