ቀጥታ፡

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርና ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር የጋራ አጀንዳችን ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስከበርና ሀገራዊ አንድነትን ማጠናከር የጋራ አጀንዳቸው መሆኑን የተለያዩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

ኢትዮጵያ በሰላማዊ መንገድ የባህር በር ባለቤትነት መብቷ እንዲከበር የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር የሀገር ሕልውናና ደህንነት፣ የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ዜጎች በጋራ የሚያራምዱት አቋም ነው።

ተለዋዋጭ በሆነው ዓለማዊ ሁኔታ ብሔራዊ ጥቅምን አስጠብቆ ለማቆየት የህዝቡ አንድነትና በጋራ መቆም ወሳኝ መሆኑም ይነሳል።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምና ሀገራዊ አንድነት መጠናከር ላይ ያለ ምንም ልዩነት በጋራ እንደሚቆሙ አረጋግጠዋል።


 

የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር አበራ በቀለ፤ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ከማስከበር ይጀምራል ብለዋል።

አንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ በመንግስት ፖሊሲዎችና አሰራሮች ላይ ልዩነቶች እንደሚኖሩ አመልክተው፤ በሀገር ብሔራዊ ጥቅም መከበር ላይ ልዩነት ሊኖረን አይችልም ነው ያሉት።

ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር በማበር የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ሊሰጥ የሚችል ማንኛውም ግለሰብ ወይም ቡድን እንደ ፓርቲ እንታገላለን ሲሉም ገልጸዋል።


 

የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጭና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ መብራቱ ዓለሙ(ዶ/ር)፤ ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር ሀገራዊ አንድነትና ፍትሃዊ ልማትን በማረጋገጥ ነው ይላሉ።

የሀገር አንድነትን በሚያጠናክሩና ከሌሎች ሀገራት ጋር ያለው ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ፓርቲያቸው አማራጮችን ይዞ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ትዴፓ) የፖለቲካ ዘርፍ ከፍተኛ አማካሪ ተሻለ ንጉሴ በበኩላቸው፤ ብሄራዊ ጥቅምን ማስከበር ከሀገር ፍቅርና ክብር ጋር የተቆራኘ ነው ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ ትልቁ ማሳያ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በህዳሴ ግድብ ላይ የነበራቸው ተሳትፎና ድጋፍ መሆኑን በመግለጽ።

ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ የባህር በር ባለቤትነት ጉዳይ ብሔራዊ ጥቅምን ማረጋገጥ መሆኑን አንስተው፤ ኢትዮጵያ በሰጥቶ መቀበል መርህ የባህር በር ባለቤትነት መብቷ እንዲከበር የድርሻቸውን እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።


 

የህብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ምክትል ሊቀ መንበር አበራ በቀለ ኢትዮጵያ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የባህር በር እንድታጣ መደረጉን ያስታውሳሉ።

ኢትዮጵያ የባህር በር እንዲኖራት ማድረግ በብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ፓርቲያቸው ድጋፉን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጭና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ሃላፊ መብራቱ ዓለሙ(ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በጥቂት የፖለቲካ ቡድኖች የተነጠቀችው የባህር በር አሁን ላይ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑ ቁጭትን ይፈጥራል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ በየዓመቱ የምታወጣው ወጪ ምርታማነትን በማሳደግ የሀገሪቱን ብልጽግና እውን ለማድረግ ተጨማሪ አቅም ይሆን ነበር ሲሉም ገልጸዋል።

ፓርቲያቸው ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ የጀመረችው ጥረት እንዲሳካ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም