ቀጥታ፡

በአካባቢያችን በሰፈነው ሰላም የልማት ጥያቄያችን ምላሽ እያገኘ ነው - የምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ ነዋሪዎች

ጊምቢ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ በአካባቢያቸው በሰፈነው ሰላም የልማት ጥያቄያቸው ምላሽ እያገኘ መሆኑን የምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።

በዞኑ ሠላምን የማጽናትና የልማት ስራዎችን የማጠናከር ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የገለጸው ደግሞ የዞኑ አስተዳደር ነው፡፡

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ አካባቢያቸውን ነቅተው በመጠበቅ የሰፈነውን ሰላም በማፅናት የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የበኩላችንን እንወጣለን ብለዋል።

የዞኑን ሰላም ከማፅናት ባሻገር በአካባቢያቸው እየተከናወኑ ባሉ የልማት ስራዎች ንቁ ተሳታፊ በመሆን ለሁለንተናዊ ብልፅግና መሳካት እንደሚተጉም ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል የላሎ አሳቢ ወረዳ ነዋሪው አቶ ጂሬኛ እንዳለ እንደተናገሩት፤ በአካባቢያቸው በሰፈነው ሰላም የልማት ጥያቄያቸው ምላሽ እያገኘ ነው፡፡ 

የሰላሙ ባለቤት ህብረተሰቡ ነው ያሉት አቶ ጂረኛ በአካባቢው የሰፈነውን ሰላም ለማፅናት የሚደረገውን ጥረት ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት እያገዙ መሆናቸውን ገልፀዋል።


 

በወረዳው የሰፈነው ሰላም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ተግባራት በፍጥነት እንዲከናወኑ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የተናገሩት ደግሞ የዚሁ ወረዳ ነዋሪው አቶ ምትኩ ሹማ ናቸው፡፡ 

ቀደም ሲል በአካባቢያቸው ተፈጥሮ በነበረው የጸጥታ ችግር የልማት ስራዎች ባሉበት ቆመው እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን በሰፈነው ሰላም ምክንያትም ነዋሪው በልማት ስራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ለዚህም በአካባቢው የሰፈነውን ሰላም ለማጽናትም ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 


 

የበጊ ወረዳ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሐነኔ ያዴሳ በበኩላቸው በአካበቢያቸው የሰፈነው ሰላም ልጆች ያለ ስጋት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማስቻሉን አስረድተዋል፡፡  

ያለ ሰላም የትኛውም ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የለም ያሉት ወይዘሮዋ ለሰላም መስፈን የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ 


 

አቶ የኑስ ኦልጂራ የተባሉ ነዋሪም በአካባቢያቸው የሰፈነው ሰላም የንግድና ማህበራዊ አንቅስቃሴያቸውን ለማቀላጠፍ ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡

 

የቤጊ ወረዳ ጸጥታ እና አስተዳዳር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተስፋ ብርሃኑ በበኩላቸው በወረዳው በጸጥታ ኃይሉና በህዝቡ ቅንጅት ሰላም መስፈኑን ጠቅሰዋል፡፡

በሰፈነው ሰላም ህብረተሰቡ ያለምንም ስጋት ተንቀሳቅሶ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን እንዲያከናውን ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡

ሰላምን በማዝለቅ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲቀጥሉም ህብረተሰቡ ከጸጥታ ኃይሉ ጋር የጀመረውን ቅንጅት እንዲያጠናክርም አሳስበዋል፡፡ 


 

የላሎ አሳቢ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ ሞላቱ ዲንሳ በበኩላቸው በወረዳው የሰፈንው ሰላም ለህብረተሰቡ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት ማስቻሉን ተናግረዋል፡፡ 

በተገኘው ሰላም በወረዳው የቡና ልማትን በማስፋትና ህገወጥ የቡና ንግድን በመቆጣጠር ህብረተሰቡን ከልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም