ቀጥታ፡

በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ወደ ሀገራቸው ለተመለሱ ከ6 ሺህ በላይ ዜጎች አስፈላጊው ማህበራዊ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ወደ ሀገራቸው ለተመለሱ ከስድስት ሺህ በላይ ዜጎች አስፈላጊውን ማህበራዊ ድጋፍ በመስጠት ከቤተሰባቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ገለጹ።

በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ ለኢዜአ እንዳሉት የኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ በመቅረፅ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ በስፋት እየተሰራ ነው።

በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚሁ ተግባር ላይ የሚሳተፉ ደላሎችን ተጠያቂ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዜጎች በሀገራቸው በሚፈጠሩ የስራ እድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑና አስፈላጊውን ማህበራዊ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ በትብብር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ ከስድስት ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱና አስፈላጊ ማህበራዊ ድጋፍ አግኝተው ከቤተሰባቸው ጋር እንዲቀላቀሉ መደረጉንም ገልፀዋል።

ዜጎች በህጋዊና ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ የሁለትዮሽ የስራ ስምምነት ወደ ተደረገባቸው ሀገራት እንዲሄዱ ዕድል መመቻቸቱን ተናግረዋል።

ዜጎች በሰው ተኮር የልማት ስራዎች በተፈጠሩ የስራ እድሎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

ዘላቂ የሆነ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን በመዘርጋት የዜጎችን የኑሮ ሁኔታ ወደተሻለ ደረጃ ለማሻገር የህብረተሰቡ ሚና ወሳኝ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም