የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ጥናት በሦስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ይፋ ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ጥናት በሦስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ ይፋ ይደረጋል
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ በዩኒቨርሲቲ እየተሰጠ ያለው የመውጫ ፈተና ውጤታማነትን አስመልክቶ እየተከናወነ ያለው ጥናት በቀጣዮቹ ሦስት ወራት ተጠናቆ ይፋ እንደሚደረግ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትምህርት ሚኒስቴር የአካዳሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ መንግስት የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ለዲግሪ ምሩቃን የመውጫ ፈተና ከ2015 ዓ.ም ጀምሮ መስጠት መጀመሩን ገልጸዋል።
በየዓመቱ እየተሰጠ በሚገኘው ፈተና እስከ 250ሺህ የሚደርሱ ተማሪዎች ፈተናውን እየወሰዱ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ፈተናው ተማሪዎች መጨረሻ የሚጠበቅባቸውን ክህሎት እና እውቀት ለመፈተሽ ያለመ መሆኑን አስታውቀዋል።
መሪ ስራ አስፈጻሚው ይህ አሰራር በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ የሚሰራበት መሆኑን ጠቅሰው፤ ሀገራትም እንደ ጥሩ ልምድ እየወሰዱት መሆኑን አብራርተዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የመውጫ ፈተና የትምህርት ጥራትን ከማረጋገጥ አንፃር ጥሩ ውጤት እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል።
ፈተናው መሰጠት ከተጀመረ ጀምሮ ተመራቂ ተማሪዎች ጨምሮ አዲስ ገቢ ተማሪዎች በቂ ዕውቀት እንዲያገኙና መምህራን ለተማሪዎች በቂ ድጋፍ እንዲያደርጉ እያስቻለ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የመውጫ ፈተናውን ውጤት በጥናት በማረጋገጥ በቀጣይ መሠራት ያለበትን ሥራ በመለየትና የአፈጻጸም ወጥነትን ለማረጋገጥ እየተጠና መሆኑን አስታውቀዋል።
የጥናቱ ዓላማ የፈተናውን ውጤታማነትና በሀገሪቱ የትምህርት ጥራት ላይ ያለውን ተፅዕኖ በጥልቀት ለመፈተሽ ያለመ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ጥናቱ በቀጣይ ሦስት ወራት ተጠናቆ ይፋ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።
በተያያዘም ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰጠው የመግቢያ ፈተና ጥሩ አፈጻጸም እንዳለው ገልጸዋል።
ፈተናው በድህረ ምረቃው የመግቢያ ፈተና ብቁ የሆኑ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ እንዲገቡ በማድረግ ለትምህርት ጥራት ሚና እየተወጣ መሆኑን አንስተዋል።
በቀጣይ ደግሞ የድህረ ምረቃ መርሃ ግብሮችን በምርምር ለመደገፍ ጥናቶች ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።