የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳሉ።
ከረፋዱ አራት ሰዓት መቻል ከይርጋጨፌ ቡና ይጫወታሉ።
መቻል በሊጉ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። አንድ ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል። ቡድኑ በ10 ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
አዲስ አዳጊው ይርጋጨፌ ቡና በውድድር ዓመቱ ባደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች አንድ ጨዋታ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪው አንድ ጨዋታ ነጥብ ተጋርቷል።
ይርጋጨፌ በአራት ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
መቻል በአምስተኛ ሳምንት አርባምንጭ ከተማን 2 ለ 0 ሲያሸንፍ ይርጋጨፌ ቡና ከአዳማ ከተማ አንድ አቻ መለያየታቸው የሚታወስ ነው።
በሌላኛው መርሃ ግብር አዳማ ከተማ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
አዳማ ከተማ በሊጉ ባካሄዳቸው አምስት ጨዋታዎች አንድ ጊዜ አሸንፎ ሶስት ጊዜ ተሸንፎ አንድ ጊዜ አቻ ወጥቷል። በአራት ነጥብ 11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ቦሌ ክፍለ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል በሁለቱ ሲያሸንፍ ሶስት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። ቡድኑ በስድስት ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል።
በአምስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር አዳማ ከተማ ከይርጋጨፌ ቡና አንድ አቻ ሲለያይ ቦሌ ክፍለ ከተማ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የ3 ለ 0 ሽንፈት አስተናግዷል።
ጨዋታው ሁለቱ ቡድኖች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።