መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር፣ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና አሰባሳቢ ትርክትን ለመገንባት በጋራ ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር፣ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና አሰባሳቢ ትርክትን ለመገንባት በጋራ ሊሰሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ሕዳር 3/2018 (ኢዜአ)፦መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር፣ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠርና አሰባሳቢ ትርክትን ለመገንባት በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ የሚያስችል አቅም ያላቸው የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞችን ለመፍጠር የኢትዮጵያ ሚዲያ ልህቀት ማዕከል ሥራ ማስጀመሩ ይታወቃል።
የልህቀት ማዕከሉ የብሔራዊ ጥቅም፣የሕብረ ብሔራዊ አንድነት፣ የወል ትርክትና ብልጽግና ላይ የጋራ አቋም ያላቸው የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትና ጋዜጠኞችን ማፍራትን ያለመ ነው።
ማዕከሉ በዛሬው ዕለትም ሁለተኛውን ዙር በመገናኛ ብዙኃንና ዲሞክራሲ ላይ የሚያተኩር ስልጠና አስጀምሯል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጂጌ (ዶ/ር)፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በሀገራዊ ዕይታ ዙሪያ ከፍ ያለ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ስልጠናው ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገር ደረጃ በሁሉም መስኮች የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎችን ጎልተው እንዲወጡ ብሎም የሕዝቡን ተጠቃሚነት ይበልጥ እንዲያረጋግጡ ባለሙያዎች በእውቀት ላይ የተመሠረተ ሥራ እንዲሠሩም ያስችላል ብለዋል።
የተጀመረው የዲሞክራሲያዊ ባህል ግንባታ እውን እንዲሆንና ልምምዱንም ሕዝቡ እንዲረዳ ከማድረግ አኳያ የልህቀት ማዕከሉ አበርክቶ ታላቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበርና ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር አንዳችም ልዩነት ሊኖራቸው እንደማይገባም ተናግረዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን ሀገርን ማሻገርና የህዝቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በሚያስችሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ ዙሪያ ሁሉም የመገናኛ ብዙሃን በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመው፥ የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነትን ጥያቄ ዙሪያ ተመሳሳይ አቋም መገንባት መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን ህብረ-ብሔራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ አሰባሳቢ ትርክት ዙሪያ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመው፥ በዲሞክራሲ ባህል እና በተቋም ግንባታ ዙሪያም በጋራ መሥራት አለባቸው ብለዋል፡፡
በሌላ መልኩም የሰላም ባህል ግንባታ እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ መገናኛ ብዙሃን በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳምሶን መኮንን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የልህቀት ማዕከሉ ብሔራዊ ጥቅምን ማዕከል ያደረገ ጋዜጠኝነትን የተካነ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ ለማፍራት ያግዛል ብለዋል።
የስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ሰላማዊት ወንድወስን እና መስፍን ፈለቀ በሰጡት አስተያየትም፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ተረድተው ማስጠበቅ እንዲችሉ ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።
ባለሙያዎቹ እንዲህ ያሉ አቅምን የሚዋጁ ስልጠናዎችን ማግኘታቸው ለተጀመረው ሀገራዊ መግባባት መፍጠር ሥራ የራሱን አዎንታዊ ሚና እንዲያበረክቱ የሚያስችላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል።