ቀጥታ፡

የተወጠኑ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ለስኬት እንዲበቁ የበኩላችንን ለመወጣት ዝግጁ ነን

አርባ ምንጭ፤ህዳር 3/2018/ኢዜአ/፦ኢትዮጵያ የወጠነቻቸው ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ ሌሎች የልማት ውጥኖች ለስኬት እንዲበቁ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ባለው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ የተሳተፉ የተለያዩ የእምነት አባቶች ገለጹ።

አስተያየታቸውን የሰጡ የሃይማኖት አባቶች እንደገለፁት፥ ኢትዮጵያ የወጠነቻቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ጨምሮ ሌሎች የልማት ውጥኖች ለስኬት እንዲበቁ የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ዝግጁ ናቸው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ዋና ኃላፊ መጋቢ ካህናት አባ ሀብተጊዮርጊስ አስራት፤ ሀገራችን በሁሉም የልማት መስኮች ትንሳኤ ላይ ትገኛለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በሀገራችን እየተከናወነ ያለው የልማት ውጥን እንዲሳካ የበኩሏን አስተዋጽኦ ስታበረክት መቆየቷንም አስታውሰዋል።

ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ነድፋ እየተጓዘች መሆኗን ጠቅሰው፥ ዘርፈ ብዙ የልማት አጀንዳዎች እንዲሳኩም ቤተ እምነታቸው የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በተለይም በመልካም ስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ በመቅረጽም የሃይማኖት ተቋማት ሚና የማይተካ በመሆኑ ቤተክርስቲያኗ የሚጠበቅባትን እንደምትወጣ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ለሚከናወኑ የልማት ትልሞች መሳካት የሃይማኖት ተቋማት ሚና ጉልህ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ተወካይ አብደላ ከድር (ዶ/ር) ናቸው።

ሙስሊሙ ማህበረሰብ ለሀገር ሰላም እና ልማት ለዘመናት አስተዋጽኦ ሲያበረክት መቆየቱን ጠቁመው፥ በሀገሪቱ የታቀዱ የልማት ስራዎች የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በመሆናቸው እንዲሳካ ድጋፋችን ይቀጥላል ብለዋል።

የኦሮሚያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ቦርድ ተወካይ መጋቢ ዮሐንስ ተስገራ “የአንድ ሀገር ዕድገት እንዲሳካ መንግስት ብቻ ሳይሆን የተለያዩ አካላት ተሳትፎና ቅንጅት ያስፈልጋል” ብለዋል።

በሀገራችን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መመረቁ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማብሰራቸው ትልቅ የህዝብ መነሳሳትና አንድነት መፍጠሩንም ተናግረዋል።

ይህ ተሳክቶ ለማየት ያጓጓል ያሉት አስተያየት ሰጪው፥ ውጥኑ ከግብ እንዲደርስ ተቋማቸው የበኩሉን እንደሚወጣ ጠቁመዋል።

የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የጋሞ ልማት ማህበር የገነባውን አርባ፤ አርባ ሁለት (40፤ 42) የተሰኘውን 1 ሺህ 680 ደረጃዎችን፣40 ምንጮችንና የአርባ ምንጭን ጥቅጥቅ ደን ጎብኝተዋል።

5ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ በነገው ዕለትም የሚቀጥል ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም