ኮርፖሬሽኑ በ20 ሺህ ሔክታር ላይ የደረሱ የምርጥ ዘር ሰብሎችን እየሰበሰበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ በ20 ሺህ ሔክታር ላይ የደረሱ የምርጥ ዘር ሰብሎችን እየሰበሰበ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 3/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ20 ሺህ ሔክታር ላይ የደረሱ የምርጥ ዘር ሰብሎችን እየሰበሰበ መሆኑን አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ የኮሙኒኬሽንና ማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራ አመራር ሥራ አስኪያጅ ጋሻው አይችሉህም ለኢዜአ እንዳሉት፥ ተቋሙ በራሱ የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻዎች እንዲሁም በኮንትራት ዘር አባዥ እርሻ (በሰፋፊ የባለሃብቶች እርሻ)፣ በክላስተር በተደራጁ አርሶ አደሮች ማሳ እና በሦስት የግብርና ቴክኒክና ሞያ ትምህርት ሥልጠና ኮሌጆች እርሻ የተባዙ ሰብሎችን እየሰበሰበ ነው።
በአጠቃላይ በ20 ሺህ ሔክታር መሬት ላይ የተባዙ የ22 ሰብሎች 90 ዝርያዎች ምርት እየተሰበሰበ ይገኛል ብለዋል።
ኮርፖሬሽኑ በ2017/18 የምርት ዘመን ለማባዛት ያቀደው 460 ሺህ ኩንታል ዘር መሆኑንም አስታውቀዋል።
በሀገር ደረጃ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማሳካት እየተደረገ በሚገኘው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ውስጥ ኮርፖሬሽኑ የግብርና ግብዓቶችንና ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን በማቅረብ እንዲሁም የተቀናጀ የሜካናይዜሽን አገልግሎት በመስጠት ግምባር ቀደም ሚና እየተጫወተ ይገኛል ሲሉም ገልፀዋል።