የኢትዮጵያ የዴሞክራሲና ፍትሕ ተቋማት ሪፎርም የቀጣናውን ሀገራት ዘላቂ ዴሞክራሲና ሰላም ታሳቢ ያደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዴሞክራሲና ፍትሕ ተቋማት ሪፎርም የቀጣናውን ሀገራት ዘላቂ ዴሞክራሲና ሰላም ታሳቢ ያደረገ ነው
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 3/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲና ፍትሕ ተቋማት ሪፎርም የቀጣናውን ሀገራት ዘላቂ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና አስተማማኝ ሰላም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
3ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ ሀገራት ፎረም "ሰላምና ደህንነትን ለማጠናከር የብሔራዊ የዲሞክራሲ ተቋማት ሚና" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው።
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢጋድ የአባል ሀገራትን አቅም በመገንባት ቀጣናዊ ትብብር ለመፍጠር ጥረት እያደረገ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት በዴሞክራሲና ፍትህ ተቋማት ላይ ያደረገቻቸው ሪፎርሞች ለዘላቂ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታና አስተማማኝ ሰላም ማስፈን ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሰላም ላበረከቱት አስተዋፅኦ የሰላም ኖቬል ሽልማት ማግኘታቸውን አስታውሰው፤ በመደመር ፍልስፍና ጠንካራ የዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋማት እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ብዝሀ የዲሞክራሲ ተቋማትን በማሻሻልና አዳዲስ ተቋማትን በመፍጠር ዕውቀት መር የመንግስት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አቅም ተገንብቷል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ባሉ የዴሞክራሲ ተቋማት ላይ የህግ ማዕቀፍ ሪፎርም ማድረጓን ተናግረዋል፡፡
ለመገናኛ ብዙሃን ምቹ ከባቢ ለመፍጠር የሚዲያ አዋጅ መውጣቱን ገልጸው፤ በፍትሕ ተቋማት ላይ የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ በጠንካራ አመራር እንዲመሩ መደረጉንም ተናግረዋል።
ሰላም የዘላቂ ተቋማት ውጤት መሆኑን የገለጹት ዶክተር ቢቂላ ፤ ኢትዮጵያ ባለፉት ሰባት ዓመታት ከራሷ አልፎ በቀጣናው ሰላምና ደህንነትን ማስፈን የሚያስችል ተቋማዊ ሪፎርም ማድረጓን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ ኢጋድ አባል ሀገርነቷ የዲሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከርና መልካም አስተዳደርን በማስፈን ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት ገንቢ ሚና እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጂኦ ስትራቴጂ ለቀጣናው ሀገራት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ የሚከናወኑ በጎም ሆነ መጥፎ ሥራዎች ተፅዕኗቸው ለጎረቤት ሀገራትም ይተርፋል ብለዋል፡፡
በዚህም ባለፉት ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ የተከናወኑ የዲሞክራሲና የፍትሕ ተቋማት ሪፎርም ነገንና የቀጣናውን ሀገራት ዘላቂ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና አስተማማኝ ሰላም ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሀገራዊ ሪፎርሞቹ በጎረቤት ሀገራት ላይ በጎ ተጽዕኖ በመፍጠር ቀጣናዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
የኢጋድ ሰላምና ደህንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ፤ ሽብርተኝነት፣ ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥና ህገወጥ እንቅስቃሴ የኢጋድ ቀጣና ፈተናዎች መሆናቸውን አንስተዋል፡፡
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለስልጣን /ኢጋድ/ ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በመተባበር የአባል ሀገራቱን አቅም የመገንባት ሃላፊነትና ግዴታ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
ዴሞክራሲ ዜጎች በነፃነት መንቀሳቀስ እንዲችሉ፣ ለሰብዓዊ መብት መከበርና ለፖለቲካ ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍ ያለ ዋጋ እንዳለው በማንሳት፤ ሀገራት በተቋማት ግንባታ ላይ ማተኮር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያ በሽግግር ፍትህና በሀገራዊ ምክክር ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲን ለመገንባት የምታደርገው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ፤ ኢትዮጵያ ከራሷ አልፎ በቀጣናው ሰላምና ደህንነት ላይ ገንቢ ሚና እየተወጣች መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ ሰውን መግንባት ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ከለውጡ በኋላ በተቋማት ግንባታ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደ ተፎካካሪ ፓርቲዎች መቀየር አንድምታው ትልቅ መሆኑን ገልጸው፤ ከለውጡ በፊት ይህ አይታሰብም ነበር ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ፀረ ሙስና ኮሚሽንና መሰል የዴሞክራሲ ተቋማትን እያጠናከረች መሆኑን በማንሳት፤ ለቀጣናው ሰላምና ደህንነት መስፈን የጎላ አበርክቶ እንዳላት ገልጸዋል፡፡