በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦በሚቀጥሉት አስር ቀናት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቅ፣ፀሐያማና ነፋሻማ የአየር ሁኔታ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ፥ በሰሜን፣በሰሜን ምስራቅ፣ በምስራቅ፣ መካከለኛው እና ደቡብ ደጋማ አካባቢዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ እንደሚቀጥል አስታውቋል።
በጋ ሁለተኛ የዝናብ ወቅታቸው የሆኑት የደቡብ፣ደቡብ ምስራቅ እና የደቡብ ምዕራብ የአገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የሚቲዎሮሎጂ መረጃዎች ያሳሉ ብሏል።
ወቅቱን ያልጠበቀ አነስተኛ መጠን ያለው ዝናብ በሰሜን፣ መካከለኛው፣ ምዕራብና ደቡብ ጎንደር ዞኖች፣ባህርዳር ዙሪያ፣ አዊ፣ በምዕራብና ምስራቅ ጎጃም፣ መተከል፣ አሶሳ፣ ካማሺ፣አርሲ፣በባሌ ዞኖች አልፎ አልፎ ሊዘንብ እንደሚችል ኢኒስቲትዩቱ ገልጿል።
በሚቀጥሉት አስር ቀናት በደቡብ ምዕራብ እና ደቡባቢ የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የሚኖረው መካከለኛ መጠን ያለው ርጥበት ለወቅቱ የግብርና ስራ እንቅስቃሴ በአመዛኙ አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረው አስታውቋል።
የበጋ ርጥበት ተጠቃሚ ተፋሰሶች መጠነኛ የገፀ ምድር የውሃ ፍሰት እንደሚኖራቸው የሚጠበቅ ሲሆን የተቀሩት ዝቅተኛ ርጥበት እንደሚኖራቸው ገልጿል።
በዚህም አብዛኛው ባሮ አኮቦ፣ መካከለኛው እና ታችኛው ኦሞ ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ አባይ እንዲሁም ገናሌ ደዋ መካከለኛ ርጥበት ያገኛሉ፡፡
አብዛኛው አዋሽ፣ዋቤ ሸበሌ፣አፋር ደናክል፣ተከዜ፣ ኦጋዴን ደግሞ ከመጠነኛ ርጥበት እስከ ደረቅ ሁኔታ ይኖራቸዋል ተብሏል።