ቀጥታ፡

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን ያጠናክራል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ሕብረ-ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ለሀገረ መንግስት ግንባታ የጎላ ሚና እንዳለው የዘርፉ ምሁራን ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ብሔሮችና ብሔረሰቦች በአንድነት፣ በወንድማማችነትና በመቻቻል የሚኖሩባት ሀገር ነች።

ይህንኑ አብሮነትና አንድነት ለማጠናከር የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በየአመቱ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ ይገኛል፡፡

ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረው በዓል "ዲሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት በሆሳዕና ከተማ ይከበራል፡፡

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን ቀኑ የሀገሪቷን ብዝኃነት፣ ውበትና ኅብረ ብሔራዊነት አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለውጡን ተከትሎ ቀኑን በማስመልከት የሚከበሩ በዓላት ለሀገረ-መንግስት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝምና አስተዳደር ጥናት ማዕከል ሃላፊና መምህር መሀመድ ደጀን (ዶ/ር) ቀኑ የህዝቦችን ማህበራዊ መስተጋብር ከማጠናከር አኳያ በርካታ ጥቅሞች እያስገኘ መሆኑን ተናግረዋል ፡፡

ኢትዮጵያ ያልተማከለ የመንግስት ሥርዓት የምትከተል በመሆኗ የህዝቦችን አብሮነትና አንድነት ለማጠናከር የቀኑ መከበር ትልቅ እገዛ እያበረከተ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተለይ ዜጎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ፣ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያላቸውን አንድነት በማጎልበት የኢኮኖሚ እድገትና ሰላምን እንዲያረጋግጡ ትልቅ እድል መፍጠሩን አብራርተዋል፡፡

በፖሊሲ ጥናት ኢኒስቲትዩት የመልካም አስተዳደር የምርምር ማዕከል አስተባባሪ እና መሪ ተመራማሪ ጥላሁን ተፈራ (ዶ/ር) በበኩላቸው ቀኑ የክልሎቹን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማሳደግ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ዕድል መፍጠሩን አስታውቀዋል፡፡

የቀኑ መከበር ለሀገረ-መንግስትና ለሰላም ግንባታ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን በመግለፅ፤ ህዝቦች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁ፣ የባህል ልውውጥ እንዲያደርጉና ማህበራዊ መስተጋብራቸው እንዲጠናከር የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም