ቀጥታ፡

 የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ህብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማፅናት አግዟል

ድሬዳዋ፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማጠናከር ጠንካራ ሀገረ መንግስት እንዲገነባ  እያገዘ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፈትህያ አደን ተናገሩ።

በድሬዳዋ 20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ህብረ ብሔራዊ አንድነትንና ልማትን በሚያፀኑ ሁነቶች ከዛሬ ጀምሮ መከበር ጀምሯል።

የአስተዳደሩ ምክርቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ፈትህያ አደን  እንደተናገሩት፤ ባለፉት ዓመታት የተከበረው የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማፅናት የሀገረ መንግስት ግንባታውን እያጠናከረ ይገኛል።

በተለይም በዓሉ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በፍቅር፣ በአንድነትና በተጋመደ ኢትዮጵያዊ መከባበር በሚኖሩባት ድሬዳዋ ዘላቂ ሰላምና ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር አበርክቶው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።

"ዴሞክራሲያዊ መግባባት-ለህብረ ብሔራዊ አንድነት" በሚል መሪ ሃሳብ ዘንድሮ ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረው በዓል በህብረ ብሔራዊ አንድነት፣ በቆራጥ ተሳትፎና ብሔራዊ ጀግንነት የህዳሴውን  ግድብ ባጠናቀቅንበት ወቅት መከበሩ ድርብ በዓል ያደርገዋል ብለዋል።

በዓሉ ይህን ተስፋ ሰጪ የልማት ጉዞ እና ድህነትን ለማስወገድ የተጀመሩና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በሚያስችሉ ሁነቶች በደመቀ መንገድ በአስተዳደሩ እንደሚከበርም አስታውቀዋል ።

በተለይም የገጠርና የከተማ ወረዳዎች፣ ተቋማት እና ነዋሪዎችን ባሳተፈ መንገድ በውይይት፣ በልማት ስራዎች እና በስፖርታዊ ውድድሮች ከዛሬ ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ይከበራል ብለዋል።

በተጨማሪም የኢፌዴሪ ህገ መንግስት መሠረታዊ ዕውቀቶችን በሚያስጨብጡ የግንዛቤ መፍጠሪያ መድረኮች እንደሚኖሩም በማስታወስ ።

የዘንድሮ 20ኛው የኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ቀን በዓል እንደ አገር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም