ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት መጎልበት የኃይማኖት ተቋማት የላቀ ሚናቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና አንድነት መጎልበት የኃይማኖት ተቋማት የላቀ ሚናቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል
አርባምንጭ ፤ ሕዳር 3/2018(ኢዜአ)፡- ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ አንድነት መጎልበት የኃይማኖት ተቋማት የላቀ ሚናቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀኃፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ተናገሩ።
"ሃይማኖቶች ለሰላም፣ለአንድነትና ለአብሮነት" በሚል መሪ ሀሳብ 5ኛው ሀገር አቀፍ የሰላም ኮንፈረንስ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጠቅላይ ፀኃፊ ሊቀ ትጉኃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ ፤ ለዘላቂ ሰላምና ለሕዝቡ አብሮነት መጠናከር የሃይማኖት ተቋማት የማይተካ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
ኮንፈረንሱ በሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና አብሮነትን ይበልጥ በማጠናከር ሁለንተናዊ እድገት ለማምጣት በሚደረገው ጥረት የሃይማኖት ተቋማትን ሚና ለማጎልበት ታልሞ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም እሴቶች ግንባታ ፣ ልማት እና ሀገራዊ አንድነትን አፅንቶ ለማስቀጠል ሚናቸው እንዲጎለብት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለውም ብለዋል።
በዚህም ተቋማቱ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና ሀገራዊ አንድነት መጎልበት የላቀ ሚናቸውን ይበልጥ ማጠናከር የሚጠበቅባቸው መሆኑን አመልክተው፤ ሁሉም ዜጋ ለሰላም መፅናት የድርሻውን እንዲወጣም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የሥራና ክህሎት ቢሮ ሃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) ፤ ሰላም ለሕዝብ ደህንነትና ለዘላቂ ልማት የማይተካ ሚና አለው ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ለክልላችን ብሎም ለሀገራችን ሰላም፣ለሕዝቡ ትስስርና ትብብር የማይተካ ሚና ተጫውተዋል ሲሉም አክለዋል።
በየአካባቢው አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የክልሉ ሕዝብ ሲያደርግ የቆየውን ትብበርና ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዞኑ ሕዝብ በ"ዱቡሻ " ባሕላዊ ሥርዓት በመታገዝ ሰላሙንና አብሮነቱን ጠብቆ ለዘመናት ኖሯል ፤ ለዘላቂ ሰላምና ብልጽግና የሃይማኖት ተቋማት ሚና ጉልህ ነው ብለዋል።
የሰላም ተምሳሌት የሆነው የጋሞ ዞን ሕዝብ ለሀገር ሰላም ፣ ዕድገትና ልማት ሲያበረክት የቆየውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠል እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል።
ሰላም በየትኛውም ዋጋ የማይተመን ሀብታችን ነው ያሉት ደግሞ የአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) ናቸው።
የሕዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰላምን በመጠበቅ በቅንጅት እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ኮንፍረንስ ላይ ከሁሉም ክልሎችና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ የሃይማኖት ጉባኤ አባላት፣የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣የባህል መሪዎችና ሌሎች አካላት እየተሳተፉ ነው።