የዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ ነው
አዲስ አበባ፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፦ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር በትብብር የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑን በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች ገለፁ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ በተለያዩ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገራቸው የመመለሱ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን መግለፁ ይታወቃል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው ባለፉት አራት ዓመታት በመካከለኛ ምስራቅ፣አፍሪካ፣ ማይናማር እና የእስያ ሀገራት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ከ500 ሺህ በላይ ዜጎች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ማድረግ መቻሉን ጠቁሟል።
በዚምባብዌ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደርና በሞሪሽየስ፣ በዛምቢያ፣ በምስራቅና ደቡብ አፍሪካ ሀገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) የኢትዮጵያ ተጠሪ ረሺድ መሀመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የውጭ ዲፕሎማሲ ከሚያተኩርባቸው ጉዳዮች አንዱ የዜጎችን ክብርና መብት ማስጠበቅ ነው።
ኤምባሲዎቹ ዜጎች ችግር ሲገጥማቸው የመከታተልና የመፍታት ስራዎችን ሲያከናውን መቆየታቸውንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ዜጎችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ወደ ሀገራቸው ለመመለስ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ባለፈው ዓመት አንድ ሺህ የሚጠጉ ዜጎችን ወደ ሀገር ቤት መመለስ መቻሉን ጠቅሰው፤ ኤምባሲው ፓስፖርት የማደስ፣ መረጃ የማረጋገጥና ተያያዠ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በባህሬን የኢፌዴሪ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ቆንስል ጄኔራል አምባሳደር ሽፈራው ገነቲ፤ ሁለቱ ሀገራት የስራ ስምሪት ስምምነት ባይኖራቸውም የዜጎች ክብርና ጥቅም እንዲከበር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም በተለያየ ምክንያት ለእስር የተዳረጉ ዜጎች ነፃ የህግ አገልግሎት እንዲያገኙና ዜጎች በህጋዊ መንገድ እንዲንቀሳቀሱና በነጻነት እንዲሰሩ አስፈላጊውን ሁሉ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
ጽህፈት ቤቱ ባደረገው ጥረት ባለፈው ዓመት ከስድስት ሺህ በላይ ዜጎች ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ ማስቻሉን አንስተው፤ ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ 291 ዜጎችን እንዲመለሱ መደረጉንም ገልፀዋል።
በዱባይና ሰሜን ኤምሬትስ የኢፌዴሪ ቆንስላ ጄኔራል ፅህፈት ቤት ተጠባባቂ ጉዳይ ፈፃሚ አስመላሽ በቀለ በበኩላቸው፤ የዜጎችን መብትና ጥቅም ለማስከበር የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በዚህም ፅህፈት ቤቱ ባለፉት ሁለት ዓመታት የፓስፖርት እድሳት፣ የውክልና እና የዳያስፖራ አገልግሎቱን በኦንላይን እየሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።
ዜጎች ከስራ ውል ጋር የተያያዙ ችግሮች ሲገጥማቸው መብታቸውን ለማስከበር ከኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ ማህበር ጋር በመተባበር እየተሰራ ነው ብለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፤ ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል ብሄራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
ከስደት ተመላሾች በሀገር ውስጥ የስራ እድል ተጠቃሚ እንዲሆኑና በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ የሚሳተፉ ደላሎች በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ሚኒስቴሩ ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ዜጎች ደህንነቱ በተጠበቀ ህጋዊ መንገድ እንዲጓዙ ግንዛቤ የማስጨበጥና ለተመላሾች የማህበራዊ አገልግሎትና የአገር ውስጥ የስራ እድል ፈጠራ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር ፍፁም አረጋ መንግስት ከተለያዩ ሀገራት ጋር ምክክር በማድረግና ስምምነት በመፈጸም የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ እየሰራ ነው ብለዋል።
በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ኤምባሲዎች የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ ማህበሮችን በማደራጀት ዜጎች የሚገጥማቸውን ችግር ለመፍታት እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።