"ከትውስታ ወደ አዲስ ተስፋ" - ኢዜአ አማርኛ
"ከትውስታ ወደ አዲስ ተስፋ"
"ከትውስታ ወደ አዲስ ተስፋ"
ብርሃኑ ፍቃዱ -ከሰቆጣ
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ሕጋዊ፣ ታሪካዊ፣ መልካዓምድራዊና ኢኮኖሚያዊ መሰረት ያለው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ ላይ ማብራራታቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የባህር በሯን ያጣችበትን የ30 ዓመታት ታሪክ ለመቀልበስ ይህን ያህል ዓመት እንደማይወስድ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችበት መንገድ ሕጋዊና ተቋማዊ መሰረት የሌለው የሚያስቆጭ ብሔራዊ ጥቅም ስብራት አካል ስለመሆኑም አንስተዋል።
አቶ መለሰ ይሄይስ እና አቶ አድማሱ ደሳለኝ፤ የኢትዮጵያ የባሕር በር የተወለዱበት ስፍራ፣ የኖሩበት ቀዬ፣ ያሳደጋቸው ማህበረሰብ ... የዘመናት ትዝታና ትውስታቸው እንደሆነ ይገልጻሉ።
ይህን የታሪካቸው አካል የሆነውን የባሕር በር ማጣትም የሁል ጊዜ ፀፀትና እንደ ሰውነት ጥላ አብሮዋቸው የሚዞር እውነታ ነው።
ከአካባቢው ርቆ ለሚገኝ ሰው ትውስታውን ሲያወራ ለሌላው ተረት ተረት፤ ለራስ ደግሞ የውስጥ ቁስል ማገርሸት ሆኖ ነው የሚሰማው ይላሉ።
ኢትዮጵያም የአሰብ ወደብንና የቀይ ባህር መዳረሻን በፖለቲካዊ ሸፍጥ ማጣቷ በቀይ ባህር ላይ እየዋኙ፣ ውሃ እየተራጩ፣ በዳርቻው ነፋሻማ ስፍራ እየተዝናኑ... ለኖሩት ለእነ መለሰ እና አድማሱ መቼም የማይረሳ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የባሕር በር ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ለአለም ማሕበረሰብ ጥያቄውን ሲያሳውቁ ተደብቆ ለቆየው ትውስታቸው አዲስ ተስፋ እንደሰጣቸውም ለኢዜአ ተናግረዋል።
አቶ መለሰ ይሄይስ በአሰብ የነዳጅ ማጣሪያ ማዕከል ለ12 ዓመታት እንዳገለገሉ በትውስታና ቁጭታቸውን ወደ ኋላ ተመልሰው ያወሳሉ።
አሁን በሰቆጣ ከተማ የሚኖሩት አቶ መለሰ ይሄይስ ፤ የአሰብ ወደብ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማፋጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ተደማሪ አቅም ነበር በወቅቱ ይላሉ።
ይህን የአሰብ ወደብንና የቀይ ባሕር መዳረሻን በፖለቲካዊ ሴራ ኢትዮጵያ ስታጣ ይሰሩበት ከነበረው የአሰብ የነዳጅ ማጣሪያ ስራ አቁመው ወደ ትውልድ ስፍራቸው ሰቆጣ መምጣታቸውን አውስተዋል።
በራሳቸው ላይ ከደረሰባቸው የስራ እና ሃብትና ንብረት ማጣት ፣ እንግልትና ሌሎች ችግሮች በላይ ኢትዮጵያ ከባሕር በር የተነጠለችበትን ሁኔታ ሲያስቡና ሲያሰላስሉ እንደሚያስቆጫቸው ይገልጻሉ።
ኢትዮጵያ የቀይ ባሕርን በማጣት የባሕር በር ብቻ ሳይሆን የገቢና ወጭ ንግድን፣ የነዳጅ ማጣሪያ ጭምር ነው ያጣችው ያሉት አቶ መለሰ፤ አሁን ጥያቄው መነሳቱ ኢትዮጵያን ወደ ቀደመ ገናናነቷ ለመመለስ ያለመ አበረታች ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል።
መንግስት ያነሳው የባሕር በር ጥያቄም የዘመናት ቁጭታችንን፣ ብስጭታችንን እና ህልማችንን ከተደበቀ ትውስታ፤ ወደ አዲስ ተስፋ የወሰደ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ህጋዊና ታሪካዊ ነው ያሉት አቶ መለሰ ፤ ጥያቄው በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝም ለአዲሱ ትውልድ በማስተማርና ግንዛቤ በመፍጠር የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።
ከ1973 ዓ.ም ጀምረው ለአስር ተከታታይ ዓመታት በአሰብ ወደብ የሲቪል መሃንዲስ ክፍል ሰራተኛ እንደነበሩ ያወሱት አቶ አድማሱ ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ የባሕር ባር ባለቤት በሆነችባቸው ዘመናት ገናና እና የተከበረች ሀገር ሆና መቆየቷን አንስተዋል።
የባሕር በሩ የኢትዮጵያ የገቢና ወጭ ንግድ የሚሳለጥበት እንደነበር አስታውሰው፤ ይሄን ታላቅ ትሩፋትና ፀጋ ለማስመለስ የተጀመረው እንቅስቃሴ ቁጭትና ትውስታችንን ወደ አዲስ ተስፋ የቀየረ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በታሪካዊ ጠላቶችና ባንዳዎች እኩይ ሴራ የባሕር በር ካጣች ወዲህ ጥያቄውን ማንሳት የማይቻልበት የአፈናው ዘመን አክትሞ በለውጡ መንግስት መነሳቱ አበረታችና ለማስመለስም ከፍተኛ መነቃቃት የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።
እኔም ባለኝ አቅም ሁሉ ስለባሕር ባር አስፈላጊነት፣ ጥቅምና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ግንዛቤ በመፍጠር ለስኬታማነቱ የድርሻዬ እወጣለሁ ሲሉም ገልጸዋል።