የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ስድስተኛ ሳምንት ዛሬ ይጀመራል
አዲስ አበባ ፤ ህዳር 3/2018(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የአምስተኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ሸገር ከተማ እና ድሬዳዋ ከተማ ይጫወታሉ።
የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ከቀኑ 7 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።
አዲስ አዳጊው ሸገር ከተማ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሶስት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል።
ቡድኑ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በዘጠኝ ነጥብ አራተኛ ደረጃን ይዟል።
ተጋጣሚው ድሬዳዋ ከተማ በሊጉ ካደረጋቸው አምስት ጨዋታዎች መካከል ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ነው። በቀሪ አራት ጨዋታዎች ሽንፈት አስተናግዷል።
ድሬዳዋ ከተማ በሶስት ነጥብ 12ኛ ደረጃን ይዟል።
ጨዋታው ሸገር ከተማ ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ፣ ድሬዳዋ ከተማ ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ የሚያደርጉት ነው።
በአራተኛ ሳምንት መርሃ ግብር ሸገር ከተማ አዲስ አበባ ከተማን 3 ለ 0 ሲያሸንፍ ድሬዳዋ ከተማ በሃዋሳ ከተማ የ2 ለ 0 አስተናግዷል።
የስድስተኛ ሳምንት መርሃ ግብር እስከ ህዳር 7 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
በተያያዘም የወቅቱ የሊጉ አሸናፊ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሶስተኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታውን ዛሬ ከረፋዱ አራት ሰዓት ላይ ከአርባምንጭ ከተማ ያደርጋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በካፍ ሴቶች ሻምፒዮንስ ሊግ የሴካፋ ዞን ማጣሪያ ምክንያት በሊጉ የመጀመሪያ ሶስት ጨዋታዎቹን አላደረገም። ጨዋታዎቹም በተስተካካይ መርሃ ግብርነት ተይዘዋል።
ከተስተካካይ ጨዋታዎቹ የመጀመሪያውን ከአርባ ምንጭ ከተማ ጋር ያደርጋል።
ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስድስት ነጥብ አምስተኛ፣ አርባምንጭ ከተማ በአንድ ነጥብ የመጨረሻውን 14ኛ ደረጃን ይዟል።
ንገድ ባንክ ቀሪ ተስተካካይ ጨዋታዎቹን ከሲዳማ ቡና እና ሸገር ከተማ ጋር በቀጣይ በሚገለጹ ቀናት የሚያደርግ ይሆናል።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ15 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን ዳግማዊ ሰለሞን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ በዘጠኝ ጎሎች ትመራለች።
ብርቄ አማረ ከመቻል እና መሳይ ተመስገን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተመሳሳይ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር ይከተላሉ።