ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፉን ጉባዔ ለማስተናገድ ከአፍሪካ ሙሉ ድጋፍ አገኘች

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2018(ኢዜአ)ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ እንድታስተናግድ ከአፍሪካ ሀገራት ሙሉ ድጋፍ አግኝታለች።

በብራዚል ቤሌም እየተካሄደ የሚገኘው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ መደበኛ ጉባዔውን እያካሄደ ነው

አስቀድሞ በመሪዎች ስብሰባ በጀመረው ጉባዔ ላይ ኢትዮጵያ 32ኛውን የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን በአዲስ አበባ ለማዘጋጀት ፍላጎቱም ዝግጁነቱም እንዳላት መግለጿ ይታወሳል።

አስቀድሞ በርካታ የጎንዮሽ ውይይቶችን ሲያካሂድ ቆይቶ፥ ቴክኒካዊ ድርድርና ውይይቶችን በሚያስተናግደውና ትላንት በጀመረው ጉባዔ ላይ የኢትዮጵያን ጥያቄ የአፍሪካ ሀገራት መስማማታቸውን ይፋ ማድረጋቸውን የኢቢሲ ዘገባ ያመላክታል

የወቅቱ የአፍሪካ ተደራዳሪዎች ቡድን ሊቀመንበር በሆነችው ታንዛኒያ በኩል የኢትዮጵያ ጥያቄ ተቀባይነት ማግኘቱ ተገልጿል።

ይህንኑ አስመልክቶ በጉባዔው ንግግር ያደረጉት በብራዚል ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ኢትዮጵያ ጉባዔውን ለማስተናገድ ያቀረበችውን ጥያቄ አፍሪካውያን በመደገፋቸው ኢትዮጵያ ትልቅ አክብሮት አላት፣ እንደምታሳካው መተማመናቸውም አስደሳች ነው፣ ለዚህም ኢትዮጵያ ታመሰግናለች ማለታቸውንም አስነብቧል።

አዲስ አበባ እንግዶቿን በሚመጥን ደረጃ ጉባዔውን ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኗን ያረጋገጡት አምባሳደሩ፥ ለኢትዮጵያ ጥያቄ ሌሎች ሀገራትም ድጋፍ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ ዳፋን ለመከላከል እየወሰደቻቸው ያሉ ተግባራዊ እርምጃዎች፣ አዲስ አበባ 2ኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔን ጨምሮ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንሶችን በስኬት ማስተናገዷ፣ እንዲሁም በሁሉም ረገድ ያላትን ዝግጁነት በመግለጽ ጥያቄዋን ለዘንድሮው ጉባዔ በይፋ ማቅረቧ ይታወሳል።

አምባሳደር ልዑልሰገድ ታደሰ ኢትዮጵያ አሁንም የአየር ንብረት ለውጥን የመቋቋም ተግባራዊ እርምጃዎችን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

ጉባዔውን ለማስተናገድ ኢትዮጵያ ያቀረበችው ጥያቄ በቀጣይ ሂደቶች ተቀባይነት ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም