ቀጥታ፡

" መሬት እና ፍትህ" - የአፍሪካ ሁሉን አቀፍ የእድገት ጉዞ

መሬት በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ትርጉም ያለው ነው። መሬት ከአፍሪካውያን የአኗኗር ዘይቤ፣ ማንነት፣ ባህል እና ማህበራዊ መስተጋብር ጋር የተቆራኘ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። ከቅኝ ግዛት ዘመን በፊት የአፍሪካ በርካታ ማህበረሰቦች መሬት በልማዳዊ እና ባህላዊ ስርዓት ያስተዳድሩ ነበር።

የቤተሰብ ጎሳዎች ወይም ማህበረሰቦች መሬት የመጠቀም፣ የማስተዳደር እና ባህላዊ መንገዶች  በሰጣቸው መብት ሲያስተላልፉ ቆይተዋል። በእንደዚህ አይነት ስርዓት ውስጥ መሬት ከሀብት ባለፈ ከማህበራዊ ግንኙነቶች፣ መንፈሳዊ መስተጋብሮች እና የተፈጥሮ ሀብቶችን በጋራ የማስተዳደር ኃላፊነት ጋር ትስስር አለው።


 

በቅኝ ግዛት ዘመን የአውሮፓ ኃይሎች በስምምነቶች፣ በአዋጆች እና ኃይል በመጠቀም መሬት የቁጥጥር፣ የብዝበዛ እና ሀብትን የመንጠቂያ መሳሪያ አድርገውታል። መሬት ፖሊሲ ኃይልን ማጠናከሪያ እና የኢኮኖሚ ብዝበዛ መንገድ ሆኗል። አፍሪካውያን በልማዳዊ እና ባህላዊ መንገዶች  የነበራቸውን የመሬት መብቶች በመንጠቅ ከአፍሪካ ውጪ የሚገኙ ዜጎች ከፍተኛ የሰፈራ ፕሮግራም ማካሄጃ እንዲሆኑ በር ከፍቷል። በዚህም ከፍተኛ የሆነ የአፍሪካ ሀብት ሲበዘበዝ ቆይቷል። ሀገር በቀል ማህበረሰቦች ከመሬታቸው የመፈናቀል እና የመገለል ሰለባ ሆነዋል።

በቅኝ ገዢዎች የወጡ የመሬት ፖሊሲዎች፣ የመሬት ምዝገባ  እና የመሬት አስተዳደር ስርዓት የአፍሪካ መሬት ተጠቃሚዎችን መብት የነፈገ ነበር። የቅኝ ግዛት የቀረጸው የመሬት አስተዳደር ስርዓት አፍሪካውያንን ህጋዊ የመሬት ባለቤትነትን ያሳጣ ነው።


 

የአፍሪካ ሀገራት ከነጻነታቸው በኋላ እኩልነት ያልተረጋገጠባቸውን የመሬት መብቶች እና ስርዓቶች ወርሰዋል። ሀገራት የመሬት ፖሊሲዎቹን አሁን ያሉ የልማት ግቦችን፣ የፍትህ ፍላጎቶች እና ወቅታዊ የአስተዳደር ማዕቀፎች ባማከለ ሁኔታ የመቀየር ስራ በማከናወን ላይ ናቸው።

በቅኝ ግዛት ዘመን የመሬት መብታቸውን ላጡ ዜጎች በተለይም ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች እየተመለሰላቸው ይገኛል። ይሁንና የቅኝ ግዛት የመሬት ቅድሚያ መጥፎ፣ በሀገራት ብሄራዊ ህግ ውስጥ ያሉ የተደባለቁ የህግ ማዕቀፎች (ለምሳሌ ልማዳዊ ህጎች ከመደበኛ ህጎች ጋር መደባለቅ) እና የተቋማት የአስተዳደር ስርዓት አለመናከር በአፍሪካ ፍትሃዊ እና እኩልነት የመሬት ስርዓት የማስፈን ጉዞ ላይ ጋሬጣ ሆኗል።

ዛሬ ላይ አፍሪካ አጀንዳ 2063 እና ዘላቂ ልማት ግቦች እየተገበረች ትገኛለች። የአህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ አጀንዳዎች አንኳር ምሰሶ ተደርገው ከሚጠቀሱት ጉዳዮች መካከል አንዱ መሬት ነው። እኩል የመሬት መብት የምግብ ዋስትና እና ስርዓተ ጾታ እኩልነትን ለማረጋገጥ፣ ለከባቢ አየር ጥበቃ እና ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወቱ የአጀንዳ 2063 ሰነድ ያስረዳል።

የአፍሪካ ህብረት ከተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) እና የአፍሪካ ልማት ባንክ በመተባበር በአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ላይ ማዕቀፎች እና የህግ አሰራሮችን በመቅረጽ እያስተዋወቁ ይገኛሉ። የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የመሬት ህጎችን የተሰናነሰኑ እንዲሆኑና የተቋማት አቅምን እንዲያጠናክሩ ጥሪ በማቅረብ ላይ ነው።


 

“የመሬት አስተዳደር፣ ፍትህ እና ካሳ ለአፍሪካውያን እና ለዘርዓ አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ ስድስተኛው የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ኮንፍረንስ ከህዳር 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

ኮንፍረንሱን ያዘጋጁት የአፍሪካ ህብረት፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) በጋራ በመተባበር ነው።

ከአፍሪካ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ታሪካዊ እና የአካባቢ ጉዳዮች ጋር የተጣጣሙ እና ለነባራዊ እውነታዎች ምላሽ የሚሰጡ የመሬት ፖሊሲ ምርጥ ተሞክሮዎች በኮንፍረንሱ ላይ እየቀረቡ ይገኛል።

ህዳር 1 በነበረው የጉባኤው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸኃፊ ክላቨር ጋቴቴ በአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ጉዳይ ላይ የሚመክረው ስብሰባ በወሳኝ ወቅት የተዘጋጀ ነው ብለዋል።


 

አፍሪካውያን ያላቸውን ሰፊ የመሬት ሀብት በቅኝ ግዛት አሰራሮች ሳቢያ በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው በአፍሪካ መሬት ዛሬም የግጭትና የኢ-ፍትሐዊነት መገለጫ ሆኗል ብለዋል።

በአፍሪካ የመሬት አስተዳደር በሴቶች፣ በወጣቶችና በዝቅተኛ አርሶ አደሮች ዘንድ ኢ-ፍትሐዊነትን በማንገስ ሰፊ የኢኮኖሚ ልዩነት መፍጠሩን ገልጸዋል።

የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ስብሰባ ከአፍሪካ ሕብረት 2025 "የማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያን እና ዘርዓ አፍሪካውያን" መሪ ሀሳብ ጋር የተጣጣመ መሆኑን አንስተው፤ ዓላማው አፍሪካውያን ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው ብለዋል።

የአፍሪካውያንና ዘርዓ አፍሪካውያን የካሳ ጥያቄ ያለፈውን ማስመለስ ሳይሆን አሁን ባለው የዓለም የፋይናንስ ስርዓት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሆነ ገልጸዋል።

አፍሪካ 65 በመቶ ያልታረሰ መሬት፣ ከዓለም ኢንዱስትሪ ሁለት በመቶ ብቻ ድርሻ ያላት፣ ለአየር ንብረት ለውጭ ተፅዕኖ ያላት ድርሻ ከአራት በመቶ በታች የሆነ አህጉር መሆኗን አንስተዋል።

በአፍሪካ የመሬት አስተዳደር ስርዓቱን በማዘመን ፍትሐዊነትን ማስፈን ጊዜው አሁን ነው ያሉት ዋና ጸኃፊው፣ ሴቶችን ወጣቶችና ዝቅተኛ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ዘላቂ ሰላም ማስፈን እንደሚገባ ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የዜጎችና ዳያስፖራ ዳይሬክተር አምር አልጆዋሊ የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ የአህጉሪቱን መፃኢ ጊዜ ለመቀየር ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በአፍሪካና ዘርዓ አፍሪካውያን ላይ የደረሰው በደል ዕውቅና ማግኘት እንዳለበት ገልጸው፤ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ለሕብረቱ መሪ ሀሳብ ትግበራ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የመሬት አስተዳደር የፍትሐዊነት ምልክት መሆኑን በማንሳት፤ የመሬት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መስፈን አለበት ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 በማሳካት አካታች ብልፅግናና ሰላምን ለማረጋገጥ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።

ሕብረቱ በመሬት አስተዳደር ዙሪያ ግልፅ አሰራር እንዲሰፍን ለአባል ሀገራት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አንስተዋል።

ስድስተኛው የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ኮንፍረንስ እስከ ህዳር 5 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።

ውጤታማ እና ተጠያቂነት የሰፈነበት የመሬት አስተዳደር ስርዓት መገንባት፣ ተቋማዊ አቅምን መፍጠር እና የቁጥጥርና ክትትልን ማጠናከር በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ምክክር እንደሚደረግ  የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል።

የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት የቅኝ ግዛት አሻራዎች እና ወቅታዊ የኢ-ፍትሃዊነት ጉዳዮች  በመሬት ባለቤትነት እና አስተዳደር ያሳደሯቸውን ተጽእኖዎች ለመፍታት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ይገልጻሉ።

በመሬት ፖሊሲ ቀረጻ፣ ትግበራ እና ቁጥጥር አቅምን መገንባት፣ የእውቀት ሽግግርን ማሳደግ እና የፖሊሲ ቁርጠኝነትን ወደ ሚጨበጥ የተግባር ምላሽ የመቀየር ጉዳይም አጽንዖት የሚሰጣቸው አጀንዳዎች መሆናቸውን ህብረቱ ገልጿል።


 

በአህጉራዊ ኮንፍረንሱ ላይ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራት፣ የህብረቱ ተቋማት እና አደረጃጀቶች ከፍተኛ አመራሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የፖሊሲ ባለሙያዎች፣ የማህበረሰብ መሪዎች፣ ትውልደ አፍሪካውያንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ኮንፍረንስ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ሁነት ነው።

የመሬት ፖሊሲ ጉባኤው አፍሪካውያን ፍትሃዊ እና ዘላቂ የመሬት አስተዳደርን ለማስፈን ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነታቸውን እያሳዩበት የሚገኝ መድረክ ነው። ጉባኤው አፍሪካውያን ከባለፈው ታሪክ በመማር ፖሊሲ፣ ጥናት  እና የማህበረሰብ ድምጾችን በማቀናጀት ረገድ ያለው ፋይዳ ወሳኝ ነው።

ጉባኤው የመሬት ፍትህን የማስፈን፣ አይበገሬነትን የመገንባት እና ለሁሉም አፍሪካውያን የጋራ ብልጽግና የማረጋገጥ የጋራ ራዕይ በመደገፍ ረገድ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም