ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ህብረ-ብሔራዊ እውነተኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት እንዲገነባ ጉልህ ሚና እያበረከተ ነው

አዲስ አበባ፤ ህዳር 2/2018(ኢዜአ)፦ ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የተከበሩ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ህብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከርና እውነተኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት እንዲገነባ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኀብረ-ብሔራዊ አንድነት’’ በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መሪ ሃሳብ የትንተና መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡


 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በዓሉ የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፣ መሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው።

የሀገረ መንግስት ግንባታው ስኬታማ እንዲሆን የሚያስችሉ ስራዎች በመንግስት በኩል በትኩረት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ባለፉት የለውጥ ዓመታት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት እንዲጠናከር እና እውነተኛ የፌዴራሊዝም ስርዓት እንዲገነባ ጉልህ ሚና እያበረከተ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዓሉ በሚከበርበት ወቅት የኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበበት ስለመሆኑ እንደሚታይበት ተናግረዋል።

በዓሉን ስኬታማ ለማድረግም በርካታ ዝግጅቶች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመው፤ ኅብረ ብሔራዊነትን ይበልጥ በሚያጠናክርና አብሮነትን በሚያጸና መልኩ እንደሚከበር ገልጸዋል፡፡

በሚኒስትር ማዕረግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ እናትዓለም መለሰ በበኩላቸው፤ በዓሉ ትልቅ የሀሳብ ገበያና የአንድነት ማጽኛ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የተመረጠው መሪ ሐሳብም ኢትዮጵያ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ የሚገልጽ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ፋጤ ስርሞሎ፤ የተመረጠው መሪ ሀሳብ የኢትዮጵያን ሁኔታ በተጨባጥ የሚያሳይ መሆኑን አንስተው፤ በሀገር ደረጃ የተገኙ ውጤቶችን ማስረጽ እንደሚገባ ጠቁመዋል።


 

በዓሉ በህዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት እንዲጠናከር የሚያግዝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አለማየሁ ባውዲ ናቸው።

የተመረጠው መሪ ሀሳብም ከበዓል ተሻጋሪ ሀሳብ የያዘ መሆኑን ገልጸው፤ መገናኛ ብዙሃንም እንደ መሪ ሀሳብ ሁሉ ከፍ ያለ የዘገባ ስራ መስራት እንዳለባቸው አመልክተዋል።


 

በመድረኩ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ጨምሮ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዘሀራ ኡመድ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ እናትአለም መለሰ፣ የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አመራር አባላት፣ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አፈ-ጉባኤዎችና የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራር አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም