ሴክተር መስሪያ ቤቶች ዘመኑ የሚጠይቀውን ዲጂታል የክፍያ ስርዓቶችን በመጠቀም አገልግሎታቸውን ቀልጣፋና አስተማማኝ ማድረግ ይገባቸዋል - ኢዜአ አማርኛ
ሴክተር መስሪያ ቤቶች ዘመኑ የሚጠይቀውን ዲጂታል የክፍያ ስርዓቶችን በመጠቀም አገልግሎታቸውን ቀልጣፋና አስተማማኝ ማድረግ ይገባቸዋል
ሰመራ፤ሕዳር 2/2018 (ኢዜአ)፡- ሴክተር መስሪያ ቤቶች ዘመኑ የሚጠይቀውን ዲጂታል የክፍያ ስርዓቶችን በመጠቀም አገልግሎታቸውን ቀልጣፋና አስተማማኝ ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉ የአፋር ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ አፍክኤ ገለጹ፡፡
የአፋር ክልል ገንዘብ ቢሮና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰመራ ዲስትሪክት የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አፈፃፀም መመሪያ ላይ ለክልሉ ከፍተኛ አመራርና ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሄደዋል።
የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኩን የከፈቱት የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ አፍክኤ እንዳሉት ሴክተር መስሪያ ቤቶች ዘመኑ የሚጠይቀውን ዲጂታል የክፍያ ስርዓቶችን በመጠቀም አገልግሎታቸውን ቀልጣፋና አስተማማኝ ማድረግ ይገባቸዋል።
ይህም የጊዜና የገንዘብ ብክነትን በማስቀረት አስተማማኝ የሆነ አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት በክልሉ ሁሉም ሴክተር መስሪያ ቤቶች የወጣውን መመሪያ በመተግበር የዲጂታል ክፍያ ስርዓትን ማስጀመር እንደሚገባቸውም ነው ያስገነዘቡት።
የኤሌክትሮኒክስ ክፍያ አፈፃፀም መመሪያን ተግባራዊ በማድረግ ለተፈፃሚነቱ አመራሩና ባለሙያው ኀላፊነቱን በቅጡ ተረድቶ ሊወጣ እንደሚገባም እንዲሁ።
በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሠመራ ዲስትሪክት ዋና ዳይሬክተር ሰሚር አማረ በበኩላቸው የዲጂታል የክፍያ ስርዓቶችን በማስተግበር ረገድ ባንኩ ሚናውን እየተወጣ ነው ብለዋል።
በዚህ ላይ የቅንጅት ስራዎችን በማጠናከር ማህበረሰቡን ከእንግልት፣ ከጊዜና ከገንዘብ ብክነት የሚታደገውን አሰራር ለማከናወን ትኩረት ሰጥተው በኅላፊነት የሚንቀሳቀሱ መሆኑንም ተናግረዋል።
የክልሉ ፋይናንሰ ቢሮና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰመራ ዲስትሪክት አብሮ ለመስራትና በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ ለማድረግ የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል።
በመድረኩ የሴክተር መስሪያ ቤቶች ኃላፊዎችና የክፍያ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።