ቀጥታ፡

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የእውነተኛ ፌደራሊዝም ስርዓት ማሳያ መድረክ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል

አዲስ አበባ፤ሕዳር 2/2018 (ኢዜአ)፡-ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የእውነተኛ ፌደራሊዝም ስርዓት ማሳያ መድረክ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ።

በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነት እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስተናጋጅነት "ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኀብረ-ብሔራዊ አንድነት’’ በሚል መሪ ቃል የሚከበረው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል በመሪ ሃሳብ የትንተና መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።


 

በመድረኩ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፣የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዘሀራ ኡመድ፣ በሚኒስትር ማዕረግ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሀላፊ እናትአለም መለሰ፣የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ አመራሮች፣የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች አፈ-ጉባኤዎችና የኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ባለፉት 19 ዓመታት ሲከበር በቆየው በዓል አብሮነትን የሚያጎለብቱና አንድነትን የሚያጠናክሩ ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል።

በዓሉ ሕዝቦች እርስ በርስ እንዲተዋወቁ፣ መሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት እንዲነቃቃ የጎላ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ባለፉት የለውጥ አመታት ቀኑ በልዩ ሁኔታ እየተከበረ እንደሚገኝና የእውነተኛ ፌደራሊዝም ስርዓት ማሳያ መድረክ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ዘንድሮ የሚከበረው 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ በሚደረግ የማጠቃለያ መርሃ-ግብር ፍፃሜውን እንደሚያገኝ ተናግረዋል።

ክብረ በዓሉን የተሳካ ለማድረግም በርካታ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመው፤ በዓሉ ህብረ ብሔራዊነት በሚያጠናክርና አንድነትን በሚያጎለብት አግባብ እንደሚከበር አመላክተዋል።

ዘንድሮ እንደሀገር በርካታ ስራዎች የሚሰሩበት አመት በመሆኑ በዓሉን የተለየ እንደሚያደርገው ጠቅሰው፥ መገናኛ ብዙሀን የህዝቦችን አንድነት እና ትስስር የሚያጠናክሩ ተግባራትን እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።


 

በፌደሬሽን ምክር ቤት የመንግስታት ግንኙነት፣የዴሞክራሲያዊ አንድነት እና የህገ መንግስት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ጸሀፊ ባንቺይርጋ መለሰ በዓሉ በየአመቱ ህዳር 29 በተለያዩ ሁነቶች እየተከበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በበዓሉ ብሔር፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ባህላቸውን እንዲያስተዋውቁ እና ህብረ ብሔራዊነትን ለማጠናከር ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

የዘንድሮው በዓል ብሔር፣ብሔረሰቦች እና ህዝቦች አሻራቸውን ያሳረፉበትና የበሳል የአመራር ውጤት የሆነው የታላቁ ህዳሴ ግድብ የተመረቀበት ዓመት መሆኑ የተለየ ያደርገዋል ብለዋል።

በተጨማሪም ከመቸውም ጊዜ በላይ መጻኢ እድላችንን የምንወስንበት በመሆኑ በዓሉ በተለየ ሁኔታ እንደሚከበር ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም