አሰብ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት መሆኑን ስለምናምን የባህር በር ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት በሙሉ አቅም እንደግፋለን-አርዱፍ - ኢዜአ አማርኛ
አሰብ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት መሆኑን ስለምናምን የባህር በር ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት በሙሉ አቅም እንደግፋለን-አርዱፍ
ሰመራ፣ህዳር 2/2018 (ኢዜአ) አሰብ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት መሆኑን ስለምናምን የባህር በር ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት በሙሉ አቅም እንደግፋለን ሲሉ የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (አርዱፍ) ምክትል ሊቀመንበር አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት መሆን እንዳለባት አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸው ይታወቃል።
በመሆኑም የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት እውን ለማድረግ ሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረው፥ ጉዳዩ ምላሽ እንደሚያገኝም አረጋግጠዋል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት የአፋር አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባር (አርዱፍ) ምክትል ሊቀ መንበር አቶ መሐመድ አወል ወግሪስ፣ ኢትዮጵያ የባህር በር የነበራትና የአሰብ ወደብ ባለቤት የነበረች ሀገር ናት ይላሉ።
የቀደመ ታሪክን አጣቅሰው የሚናገሩት አቶ መሐመድ የአሰብ ራስ ገዝ አስተዳደር ሲመሰረት የአፋር ህዝብን ጥያቄ በመመለስ አሰብን በመቀመጫነት የሰየመ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ከዚህ በኋላ በተደረገው የስርዓት ለውጥ የሽግግር መንግስት ግልፅነት በጎደለው አካሄድ ኤርትራ በሪፈረንደም እንድትነጠል መደረጉን ገልጸዋል።
ያኔ በቻርተሩ መሠረት እንደ አፋር አባት የሚቆጠሩት ሱልጣን አሊሚራህ ሐንፈሬ ውሳኔውን በፅኑ ተቃውመው እንደነበረም አስታውሰዋል።
በዚህ ወቅትም የኢትዮጵያ መንግስት የባህር በር ባለቤትነትን አገራዊ አጀንዳ ማድረጉ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ የግድ የባህር በር ያስፈልጋታል ብለዋል።
በተለይም አሰብን ማጣት የኢትዮጵያ ህዝብ ለትልቅ ጉዳት የዳረገ መሆኑን አስታውሰው አርዱፍ፥ አሰብ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ግዛት ስለሆነ መመለስ እንዳለበት ያምናል ነው ያሉት።
አርዱፍ በወቅቱ አሰብን ማጣት አደገኛ ውሳኔ መሆኑን እንደሚያምንም ጠቁመዋል።
የባህር በር የማግኘት እና አሰብን የማስመለስ ጉዳይ የአፋር ህዝብና በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ሃይሎች የጋራ አቋም ጭምር መሆኑንም አቶ መሐመድ ገልፀዋል።
''ታሪክንም ሆነ ሌሎች ማስረጃዎችን ብናጣቅስ አሰብ የኢትዮጵያ ነው'' የሚሉት አቶ መሐመድ ''አሰብ ወደ ቀድሞ ግዛቱ እንዲመለስ የሚጠበቅብንን እንወጣለን'' ብለዋል።
እንደ አቶ መሐመድ ገለጻ፥ በአሰብ አካባቢ የሚገኙ አፋሮች በከፍተኛ ጫና እና እንግልት ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው የአሰብ መመለስ ለአፋር ህዝብና ባጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ ትርጉም አለው።