ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑና ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንዲያስችሉ ትኩረት ተደርጓል - ኢዜአ አማርኛ
ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑና ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንዲያስችሉ ትኩረት ተደርጓል
አዲስ አበባ፤ህዳር 2/2018(ኢዜአ)፦መንግስት ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሆኑና ተጨማሪ ገቢ ማግኘት እንዲያስችሉ ትኩረት ማድረጉን የከተማ እና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ።
10ኛው የከተሞች ፎረም ከህዳር 6 እስከ 10 በአፋር ክልል ሰመራ ሎጊያ ከተማ ይከበራል።
የበዓሉን አከባበር አስመልክተው የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም፥ በ10ኛው የከተሞች ፎረም ከ150 በላይ ከተሞች የሚሳተፉበት ሲሆን ከጎረቤት ሀገራት የሚመጡ የእህት ከተሞች የስራ ሃላፊዎችም እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
"የከተሞች ዕድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት" በሚል መሪ ሐሳብ የሚከበረው ይህ በዓል መንግስት ከተሞችን ለማዘመን እያከናወናቸው ያሉ ጉዳዮች ተነስተው ምክክርና የልምድ ልውውጥ ይካሄድባቸዋል ብለዋል።
የከተሞች መለወጥ የሀገር ዕድገት ማሣያ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ አሁን ላይ በርካታ ከተሞች በመነቃቃት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የከተሞችን መሠረተ ልማት ለማሟላት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ጠቁመው፤ የኮሪደር ልማትን ለአብነት ጠቅሰዋል።
የኮሪደር ልማት ስራዎች ከ73 በላይ በሆኑ ከተሞች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ መንግስት ከተሞች ለነዋሪዎች ምቹና ተጨማሪ ገቢ ማግኘት የሚያስችሉ እንዲሆኑ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በፎረሙ ከተሞች ከአስር ዓመት የልማት ዕቅድ አኳያ እያከናወኑ ያሉት ተግባራት ተነስተው ውይይት እንደሚካሄድባቸውም ጠቁመዋል።