በባሌ ዞን ለቡና ምርታማነትና ጥራት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በባሌ ዞን ለቡና ምርታማነትና ጥራት ትኩረት ተሰጥቷል
ሮቤ፤ህዳር 2/2018(ኢዜአ)፦በባሌ ዞን የቡናን ምርታማነት በማሳደግ ጥራት ያለው ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ገለፀ።
ለቡና ልማት ምቹ ሥነ ምህዳር ካላቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ ባሌ ነው።
ዞኑ የተሻለ ዝርያ ካለው የጫካ ቡና በተጨማሪ ከግብርና ምርምሮች የተገኙ የቡና ዝርያዎችንም በስፋት በማልማት ለማዕከላዊ ገበያ በማቅረብም ይታወቃል።
የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ጌታቸው አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በዞኑ የቡና ምርታማነትና ጥራትን በማስጠበቅ የተሻለ ምርት ለማዕከላዊ ገበያ ለመላክ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው።
ለዚህም ከልማቱ ባልተናነሰ በቡና አሰባሰብና ክምችት የሚስተዋሉ ግድፈቶችን ለማረም ለአርሶ አደሮችና ባለድርሻ አካላት ሥልጠና መሰጠቱን አስታውሰዋል።
የቡና ምርታማነትን ለማሳደግ ከ2 ሺህ 500 ሄክታር ባላይ ያረጁ የቡና ተክሎችን የመጎንደልና በአዲስ ችግኞች የመተካት ሥራ መከናወኑን አመልክተዋል።
አርሶ አደሩ የቡና ጥራትን ለማስጠበቅም ቀይ ቡና ብቻን እንዲለቅም፣ በሽቦ አልጋ አሊያም በሲሚንቶ በተሰራ ዐውድማ ላይ እንዲያደርቅም ግንዛቤ መሰጠቱን አንስተዋል።
በዞኑ ቡና አብቃይ ወረዳዎች ከ26 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች በቡና ልማቱ በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ በጽህፈት ቤቱ የቡናና ፍራፍሬ ልማት ቡድን መሪ አቶ ወንዶሰን ነጋ ናቸው።
በተለይም ምርታማነቱ እንዲጨምር ከሄክታር ይገኝ የነበረን ከ9 ነጥብ 2 ኩንታል ወደ 10 በማሳደግ በምርት ዘመኑ 437 ሺህ ኩንታል ቡና በማምረት 15ሺህ ቶን ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ ወደ ተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
በልማቱ ከተሰማሩ የደሎ መና ወረዳ አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሁሴን አብደላ በሰጡት አስተያየት በቡና አመራረት ላይ የተሰጣቸው በተግባር የተደገፈ ሥልጠና በምርት ሂደቱ ላይ አዎንታዊ ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።
መንግሥት የተሻሻሉ የቡና ዝርያዎችን እንዲያገኙ ከማድረግ በተጓዳኝ በአመራረት ሂደትም ቀይ ቡናን ብቻ በመልቀም ጥራት ያለው ቡና ለገበያ እንድናቀርብ ድጋፍ እየተደረገልን ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የልማቱ ተሳታፊ ማህሙድ በከር ናቸው።
በባሌ ዞን ከ68 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በቡና ተክል የተሸፈነ መሆኑን ከዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመክታል።
በዞኑ ባለፈው ዓመት ከ376 ሺህ በላይ ኩንታል ምርት የተገኘ መሆኑን ገልፀው ከዚህ ውስጥ የተሻለ መጠንና ጥራት ያለው ቡና ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን አስታውሰዋል።