የፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ.ዴሌቦ የቀብር ስነስርዓት ነገ ይፈጸማል - ኢዜአ አማርኛ
የፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ.ዴሌቦ የቀብር ስነስርዓት ነገ ይፈጸማል
አዲስ አበባ፤ ሕዳር 1/2018(ኢዜአ)፦ የፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ.ዴሌቦ ስርዓተ ቀብር ነገ ይፈጸማል።
ኢዜአ ከቤተሰባቸው ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ነገ 5:00 ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ የአስከሬን ሽኝት ይከናወናል።
ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ ደግሞ የቀብር ስነስርዓቱ በጴጥሮስ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን እንደሚፈጸም ተገልጿል።
ፕሮፌሰር ላጲሶ በህይወት በነበሩበት ዘመን ለሀገራቸው ኢትዮጵያ እንዲሁም ለአፍሪካ የታሪክ ጥናትና ምርምር ትልቅ አበርክቶ የነበራቸው ሲሆን፤ የተለያዩ የታሪክ መፅሀፍቶችን ፅፈው ያሳተሙና በዘርፉ አንቱታን ያገኙ ታላቅ ምሁርም ነበሩ።
ፕሮፌሰር ላጲሶ የኢትዮጵያውያንን የጋራ እሴት፣ ባሕልና ቋንቋ በማውሳት የሕዝቦች ታሪክ ጎልቶ እንዲታወቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውም ተመላክቷል፡፡
ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ.ዴሌቦ ባጋጠማቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በትናንትናው ዕለት ነበር ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ።