የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሐዋላ ሥርዓትን ለማጠናከርና የፋይናንስ ተአማኒነትን ለመጠበቅ የሚያስችል የተቀናጀ እርምጃ ወሰደ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሐዋላ ሥርዓትን ለማጠናከርና የፋይናንስ ተአማኒነትን ለመጠበቅ የሚያስችል የተቀናጀ እርምጃ ወሰደ
አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሐዋላ ሥርዓትን ለማጠናከርና የፋይናንስ ተአማኒነትን ለመጠበቅ የሚያስችል የተቀናጀ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።
ብሔራዊ ባንክ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሕግ አስከባሪ አካላት ጋር በመተባበር፤ ባልተፈቀዱ የውጭ የሐዋላ ገንዘብ ማስተላለፍ ሥራዎች ላይ በተሰማሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች ላይ የተቀናጀ እርምጃ መውሰድ መጀመሩን አመልክቷል።
እርምጃዎቹ የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት በመጠቀም ድንበር ዘለል የገንዘብ ማስተላለፍ ተግባራትን በሚፈጽሙ ደላሎችና ገንዘብ አቅራቢዎች ላይ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድን የሚያካትት ነው።
እርምጃው ብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ሥርዓትን ተአማኒነት ለመጠበቅና የውጭ ምንዛሪ ፍስት በሕጋዊ፣ ግልጽና መደበኛ በሆኑ መንገዶች መከናወኑን ለማረጋገጥ የሚያደርገውን ጥረት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጿል።
ሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውሮችን ለመፈጸም መደበኛ የፋይናንስ ሥርዓትን መጠቀም የውጭ ምንዛሪ ገበያን ተአማኒነት የሚያኮስስና የሀገሪቱን የገንዘብ ሥርዓት አደጋ ላይ የሚጥል አካሄድ ነው ብሏል ባንኩ በመግለጫው።
በአንጻሩ፣ እነዚህ የማስተካከያ እርምጃዎች ሕገ ወጥ የሐዋላ ዝውውርን ለመከላከል የሚደረግ ጥረት አካል መሆናቸውን አስታውቋል።
ባንኩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የኢትዮጵያን የፋይናንስ ሥርዓት ላልተገባ ዓላማ ለመጠቀም የሚፈልጉ አካላትን በመለየት ተገቢ እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥልም ገልጿል።
እንዲሁም፣ ባንኩ የውጭ ሐዋላ ፍሰት መደበኛ አካሄድን ተከትሎ እንዲፈጸም የሚረዱ እርምጃዎችን ለማጠናከርና በባንኮችና ሕጋዊ ፈቃድ ባላቸው የገንዘብ አስተላላፊዎች አማካይነት በቂና ቀጣይነት ያለው የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት መኖሩን ለማረጋገጥ ተግቶ እንደሚሰራም እንዲሁ።
የባንኩ ጥረቶች የሐዋላ ፍሰት ተደራሽ፣ ቀልጣፋና ግልጽ በሆነ መንገድ እንዲፈጸም ለማድረግና የሀገሪቱን የኢኮኖሚ መረጋጋትና የልማት ግቦች ለማሳካት የታለሙ መሆናቸውን አስታውቋል።
ሕዝቡ ሕጋዊ የውጭ ሐዋላ አገልግሎት አቅራቢዎችን ለይቶ ማወቅ እንዲችል ብሔራዊ ባንክ ሕግን ተከትለው በውጭ ምንዛሪ ገበያ እንዲሳተፉ የተፈቀደላቸውን የሐዋላ አስተላለፊ ድርጅቶችን ስም ዝርዝር በድረ ገጽ አድራሻ ማለትም በhttps://nbe.gov.et/mta/ - ማስቀመጡን ጠቁሟል።
ባንኩ ሕጋዊ የገንዘብ ማስተላለፊያ ዘዴዎችን አጠቃቀም የሚያበረታታና ሕዝቡ በፋይናንስ ሥርዓት ላይ ያለውን ተአማኒነት የሚያጠናክር ደህንነቱ የተጠበቀ፣ ጠንካራ እና ምቹ የፋይናንስ ከባቢ ለመፍጠር ቁርጠኛ መሆኑን አመልክቷል።