ቀጥታ፡

አፍሪካ የሰብዓዊ ድጋፎችን በራሷ አቅም ለማቅረብ የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ መቀጠል ይኖርባታል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2018(ኢዜአ)፦ አፍሪካ የሰብዓዊ ድጋፎችን በራሷ አቅም ለማቅረብ የጀመረችውን ጥረት አጠናክራ መቀጠል እንደሚኖርባት ተገለጸ።

በአፍሪካ ህብረት የስደት፣ ስደተኞች እና የውስጥ ተፈናቃይ ሰዎች የልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ አምስተኛ መደበኛ ስብሰባ መካሄድ ጀምሯል። 

በዚሁ ወቅት የስደተኞችና ተፈናቃዮችን ችግሮች ለመፍታት የጋራ ቁርጠኝነት፣ ትብብርና የአገር ውስጥ መፍትሔዎች ወሳኝ መሆናቸው ተጠቁሟል።


 

ስብሰባው በአጀንዳ 2063 አቅጣጫዎች መሠረት የስደት፣ የስደተኞች እና ተፈናቃዮች ጉዳዮች ላይ የሚተገበሩ ፖሊሲዎችን እና ስትራቴጂዎችን ለማረጋገጥ ያለመ ነው።

በስብሰባው የአፍሪካ ባለሙያዎች ስደትን፣ መፈናቀልን እና ሰብዓዊ ፈተናዎችን በትብብር እና በአገር ውስጥ መፍትሔዎች ለመፍታት የጋራ ቁርጠኝነታቸውን አረጋግጠዋል። 

ባለሙያዎቹ በአህጉሪቱ ያለውን በስደት እና በመፈናቀል ምክንያት የሚመጡ ሰብዓዊ ፈተናዎችን ለማቃለል አንድነትና ቀጣይነት ያለው አቅጣጫ እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል።

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የኢኮኖሚክ ኮሚሽን ለአፍሪካ ወኪል ሄርቭ ኩአቴ በዚሁ ወቅት፣ ስብሰባው ቁርጠኝነትን ወደ ተግባር ለመለወጥ እና ስደተኞችን የሚጠቅሙ ፖሊሲዎችን ለመመልከት ያለመ ነው ብለዋል። 

ይህም አፍሪካ ለዘላቂ ልማት ያላትን ራዕይ ከፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በአህጉሪቷ ለጠንካራና ወጥ ለሆነ ዓለም አቀፍ የስደት አስተዳደር ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት ብዝሃነትና ትብብር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።


 

የዛምቢያ ሪፐብሊክ የኢሚግሬሽን መምሪያ ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የኮሚቴው የቀድሞ ሊቀ-መንበር ኢኖስ ቺቦምቤ በበኩላቸው፤ አሁን ያሉትን ፈተናዎች ለመፍታት በአፍሪካ የሚመሩ የሰብዓዊ ድጋፍ ምላሾች ያስፈልጋል ብለዋል።

ሰብዓዊ ድጋፎች ለረጅም ጊዜ በውጫዊ ሀብቶች እና ተዋናዮች ላይ ጥገኛ እንደነበሩ አንስተው፤ ይህን መፍታትና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለማቅረብ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

አፍሪካዊ ተግዳሮቶችን በአፍሪካዊ መፍትሔዎች መፍታት ይገባል ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ የሰብዓዊ ድጋፎችን በራስ አቅም የማቅረብ ጥረቶች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም ተናግረዋል። 

ኮሚቴው በበርካታ ወሳኝ ፖሊሲዎች በመወያየት የስደት፣ የስደተኞች እና የተፈናቀሉ ሰዎችን ከአጀንዳ 2063 ጋር በማጣጣም የሰብዓዊ ማዕቀፎችንና ስልቶችን ማጽደቅ እንዲሁም መደገፍ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ተጠቁሟል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም