የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በባህል፣ በስፖርት እና ኪነ-ጥበብ ልማት ዘርፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን ማጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በባህል፣ በስፖርት እና ኪነ-ጥበብ ልማት ዘርፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን ማጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤ህዳር 1/2018(ኢዜአ)፦የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር በባህል፣ በስፖርት እና ኪነ ጥበብ ልማት ዘርፍ እያከናወናቸው ያሉ ተግባራትን አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።
ቋሚ ኮሚቴው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርን የ2018 በጀት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ የሩብ ዓመቱን አፈጻጸም ሲያቀርቡ እንዳሉት፤ባለፉት ሶስት ወራት በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በ2018 በጀት ዓመት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን የሚያጠናክሩ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸውን በርካታ ኃይማኖታዊ እና ባህላዊ በዓላትን የማስተባበር ሥራ ማከናወኑን አመልክተዋል፡፡
የኪነ ጥበብ ዘርፍን በአግባቡ ለመመራት የኪነ-ጥበብ እና የሥነ-ጥበብ ፈጠራ ልማት የፖሊሲ፣ ደንብ እና መመሪያ ረቂቅ ሰነድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ በቅርቡም ስራ ላይ እንደሚውል ገልጸዋል።
በስፖርት ዘርፍም ተተኪ ስፖርኞችን ለማፍራት የተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸውን ነው የተናገሩት፡፡
በአሁኑ ወቅት የ2029 የአፍሪካ ዋንጫን ማስተናገድ የሚያስችሉ ልዩ ልዩ የስፖርት ማስፋፊያ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑም ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ ግብረ-መልሶችን መሰረት በማድረግ የባህል፣ የስፖርት እና ኪነ-ጥበብ ዘርፉን ለማሳደግ ከመቼውም ጊዜ በላይ በትኩረት እንደሚሰራ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና የስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ሚኒስቴሩ ያከናወናቸው ባህልን የማስተዋወቅ፣ የስፖርት ተሳትፎን የማሳደግ እና የኪነ ጥበብ ዘርፉን የማበረታታት ተግባራት በጠንካራ ጎን የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል፡፡
ባህል፣ ስፖርት እና ኪነ-ጥበብ ለቱሪስት መስህብነትና ለገጽታ ግንባታ ካላቸው ፋይዳ ባሻገር የሥራ ዕድል በመፍጠር፣ ማህበራዊ ትስስርን በማጠናከርና የሀገርን ገጽታ በመገንባት ረገድ ወሳኝ ሚና እንዳላቸውም አመልክተዋል።
በቀጣይም ሚኒስቴሩ ወጣቶችን በስፋት ተጠቃሚ በሚያደርጉ የባህል፣ የስፖርትና የኪነ ጥበብ ልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ አሳስበዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ለዘርፉ እድገት አስፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል፡፡