ሚኒስቴሩ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ማጠናከር አለበት - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴሩ የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ማጠናከር አለበት
አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2018(ኢዜአ)፦የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እያከናወናቸው ያሉ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን ማጠናከር እንዳለበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስገነዘበ፡፡
ቋሚ ኮሚቴው የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን ገምግሟል።
የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ባቀረቡት ሪፖርት፣ ሚኒስቴሩ ተቋማዊ የማስፈፀም አቅምን የሚያሳድጉ ተግባራትን ማከናወኑን ገልጸዋል።
በሩብ ዓመቱ 25 ሚሊዮን ወጣቶች በበጎ ፈቃድ አገልግሎት መሰማራታቸውን ጠቁመው፤ ከ55 ሚሊዮን በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
የሴቶች፣ ሕፃናት፣ ወጣቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አረጋውያን፣ ውሎና አዳራቸውን በጎዳና ላይ ያደረጉ ዜጎችን መብትና ደህንነት የሚያስጠብቁ ሥራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
ሴቶችንና ወጣቶችን ለአመራርነት የሚያበቁ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ ሚኒስቴሩ የሕፃናት ጉልበት ብዝበዛን ለመቀነስ፣ የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ያሉ ስራዎች እንዲብራሩ ጠይቋል፡፡
ጾታዊ ጥቃትን ለመቀነስ እንዲሁም ሕገ-ወጥ ፍልሰትን ለመከላከል ሚኒስቴሩ እያከናወነ ያለውን ሥራ በተመለከተ ማብራሪያ ጠይቋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከቋሚ ኮሚቴው ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እንዳሉት በቋሚ ኮሚቴው የሚደረገው ክትትልና ድጋፍ ስራዎችን በጥልቀት ለመስራት አቅም የሚሆን ነው።
ፆታዊ ጥቃት እየቀነሰ መሆኑን የሚያሳዩ የተለያዩ ጥናቶች መኖራቸውን አንስተው፤ በሚፈለገው ልክ ለማከናወን ከሚመለከታቸው ጋር በቅንጅት ይሰራል ብለዋል።
በህፃናት ጉልበት ብዝበዛና የአካል ጉዳተኞችን የስራ እድል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውንና ስራውን የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ ቅንጅትና ትብብር ይጠናከራል ብለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ በበኩላቸው፤ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል በግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ዜጎች ደህንነቱ የተጠበቀ መንገድ እንዲከተሉ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በህገ-ወጥ ተግባር የተሰማሩ ደላሎችን እንዲጠቁም እየተሰራ ነውም ብለዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማኅበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ታደለ ቡራቃ (ዶ/ር) በአብዛኛው የተቋሙ ዕቅድ 100ና ከዚያ በላይ መፈፀሙ የሚበረታታ እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበት መሆኑን ገልፀዋል።
ሴቶችን ለአመራርነት ለማብቃት የተጀመሩ ስራዎች፣ አደንዛዥ እፅና ከመጤ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል እያከናወነ ያለውን ተግባር ይበልጥ ማጠናከር እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ወጣቶችና ህፃናት የነገይቱን ኢትዮጵያ ለመገንባት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማድረግ መቻሉን ገልፀው፤ አገልግሎቱን የበለጠ ለማስፋት በትኩረት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።