ቀጥታ፡

አሁን ባለው የዓለም የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ የአፍሪካውያንን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፤ ህዳር 1/2018(ኢዜአ)፦ አሁን ባለው የዓለም የፋይናንስ ስርዓት ውስጥ የአፍሪካውያንን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸኃፊ ክላቨር ጋቴቴ ገለጹ።

የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ስብሰባ 2025 "የመሬት አስተዳደር፣ ፍትህ እና ካሳ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ አፍሪካውያን" በሚል መሪ ሀሳብ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን መካሄድ ጀምሯል።

ስብሰባው በአፍሪካ ህብረት፣ አፍሪካ ልማት ባንክ እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በጋራ ተዘጋጅቷል።

የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ዋና ጸኃፊ ክላቨር ጋቴቴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ በአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ጉዳይ ላይ የሚመክረው ስብሰባ በወሳኝ ወቅት የተዘጋጀ ነው።

አፍሪካውያን ያላቸውን ሰፊ የመሬት ሀብት በቅኝ ግዛት አሰራሮች ሳቢያ በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው በአፍሪካ መሬት ዛሬም የግጭትና የኢ-ፍትሐዊነት መገለጫ ሆኗል ብለዋል።

በአፍሪካ የመሬት አስተዳደር በሴቶች፣ በወጣቶችና በዝቅተኛ አርሶ አደሮች ዘንድ ኢ-ፍትሐዊነትን በማንገስ ሰፊ የኢኮኖሚ ልዩነት መፍጠሩን ገልጸዋል።

የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ ስብሰባ ከአፍሪካ ሕብረት 2025 "የማካካሻ ፍትህ ለአፍሪካውያን እና ዘርዓ አፍሪካውያን" መሪ ሀሳብ ጋር የተጣጣመ መሆኑን አንስተው፤ ዓላማው አፍሪካውያን ከዓለም ነባራዊ ሁኔታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ነው ብለዋል።

የአፍሪካውያንና ዘርዓ አፍሪካውያን የካሳ ጥያቄ ያለፈውን ማስመለስ ሳይሆን አሁን ባለው የዓለም የፋይናንስ ስርዓት ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአፍሪካ መሬት ፖሊሲ ማዕከል በአፍሪካ ፍትሐዊ የመሬት አስተዳደርና የዳታ አያያዝ ስርዓት በማስፈን ግጭትን መቀነስ መሆኑን አስረድተዋል።

በአፍሪካ 65 በመቶ ያልታረሰ መሬት፣ ከዓለም ኢንዱስትሪ ሁለት በመቶ ብቻ ድርሻ ያላት፣ ለአየር ንብረት ለውጭ ተፅዕኖ ያላት ድርሻ ከአራት በመቶ በታች የሆነ አህጉር መሆኗን አንስተዋል።

ስለሆነም አፍሪካን ላለፈው በደል ዕውቅና በመስጠት እና የዓለምን የፋይናንስ ስርዓት በመቀየር ፍትሐዊ ተጠቃሚ በማድረግ መካስ ይገባል ብለዋል።

በአፍሪካ የመሬት አስተዳደር ስርዓቱን በማዘመን ፍትሐዊነትን ማስፈን ጊዜው አሁን ነው ያሉት ዋና ጸኃፊው፣ ሴቶችን ወጣቶችና ዝቅተኛ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ዘላቂ ሰላም ማስፈን እንደሚገባ ገልጸዋል።

በዚህም የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በመሬት አስተዳደር ስርዓትና ዳታ አያያዝ አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

በአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን የዜጎችና ዳያስፖራ ዳይሬክተር አምር አልጆዋሊ የአፍሪካ የመሬት ፖሊሲ የአህጉሪቱን መፃኢ ጊዜ ለመቀየር ወሳኝ ምዕራፍ መሆኑን ገልጸዋል።

በአፍሪካና ዘርዓ አፍሪካውያን ላይ የደረሰው በደል ዕውቅና ማግኘት እንዳለበት ገልጸው፤ የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ለሕብረቱ መሪ ሀሳብ ትግበራ ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የመሬት አስተዳደር የፍትሐዊነት ምልክት መሆኑን በማንሳት፤ የመሬት ፍትሐዊ ተጠቃሚነት መስፈን አለበት ብለዋል።

የአፍሪካ ሕብረት አጀንዳ 2063 በማሳካት አካታች ብልፅግናና ሰላምን ለማረጋገጥ በትብብር መስራት ይገባል ብለዋል።

ሕብረቱ በመሬት አስተዳደር ዙሪያ ግልፅ አሰራር እንዲሰፍን ለአባል ሀገራት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም